የኖርዌይ መንግስት በትግራይ ለሚከናወነው የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ድጋፍ እንደሚያደርግ አስታወቀ

77

መቀሌ ጥር 29/2011 የኖርዌይ መንግስት በትግራይ ክልል እየተከናወነ ላለው የተፈጥሮ ሃብት ልማት ስራ የሚያደርገውን እገዛ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታወቀ።

በኖርዌይ ዓለም ዓቀፍ የልማት ትብብር ሚኒስትር ዳግ ኢንግ ኡልስታይን የሚመራ የልኡካን ቡድን በትግራይ ክልል የተፈጥሮ ሃብት ጥበቃ ስራ ዙሪያ ከክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳደር ጋር ተወያይቷል።

ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት በኢትዮጵያ በተለይም በትግራይ ክልል የአካባቢ ተፈጥሮ ሃብትን መልሶ ለማልማት የሚደረገው ጥረት አበረታች ውጤት የታየበት መሆኑን ተገንዝበዋል።

በዚህም በመንግስታቸው ለዚሁ ተግባር እንዲውል በየዓመቱ የሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

የትግራይ ክልል ምክትል ርእሰ-መስተዳድር ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል በበኩላቸው “የኖርዌይ ድጋፍ በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ሳቢያ የተጎዱ አካባቢዎች በተጨባጭ መልሰው እንዲድኑ አስችሏል” ብለዋል።

ህዝቡ አካባቢውን ለማልማትና ኑሮውን ለማሻሻል በሚያርገው ርብርብ አሁንም ከጎኑ እንደማይለዩ ባለሙሉ ተስፋ መሆናቸውን ደክተር ደብረፅዮን ገልፀዋል።

የክልሉ እርሻና ገጠር ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ክፍሎም አባዲ በበኩላቸው የኖርዌይ መንግስት በየዓመቱ ለተፈጥሮ ሃብት ልማት የሚውል ከ60 ሚልዮን ብር በላይ ድጋፍ እያደረገ ለአምስት ዓመታት መጓዙን ተናግረዋል።

በድጋፉ አማካኝነት በ13 ወረዳዎች ውስጥ የነበረ የተራቆተ አከባቢ መልሶ በደን እንዲሸፈን ማስቻሉንም አስረድተዋል።

የልኡካን ቡድኑ አባላት ዛሬና ነገ በመቀሌና በእምባ አለጀ ወረዳዎች አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ማህበራዊ ተቋማትና የገጠር ልማት ስራዎችን እንደሚያዩ ለማወቅ ተችሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም