ኢዜአ እያደገ የመጣውን ፈጣን የመረጃ ፍላጎትን መመለስ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ ነው

91

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲ (ኢዜአ) በአገሪቱ እያደገ የመጣውን ፈጣን የመረጃ ፍላጎትን መመለስ የሚያስችሉ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።

ኤጀንሲው ይህን  ያለው "ትክክለኛና ወቅታዊ መረጃ ለዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ" በሚል መሪ ሃሳብ ከህዝብና ከግል መገናኛ ብዙሃን ተቋማት ሃላፊዎችና ተወካዮች ጋር ዛሬ ባካሄደው የውይይት መድረክ ላይ ነው።

በውይይት መድረኩ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት መምህር ዶክተር ተሻገር ሽፈራውና የኢዜአ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰይፈ ደርቤ ለመወያያ የሚሆኑ ጽሁፎችን አቅርበዋል።

ተቋሙ በተደጋጋሚ እንዲፈርስና መልሶ እንዲቋቋም መደረጉ፣ መረጃን በተገቢው ፍጥነት አለማድረስ፣ ከክፍያና ጥቅማጥቅም ማነስ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥም የሰራተኞች ፍልሰት፣ መገናኛ ብዙሃን ምንጭ ሳይጠቅሱ የኢዜአን ዜና መጠቀም የተቋሙ ማነቆዎች እንደሆኑ በቀረቡት ጽሁፎች ተገልጿል።

በመድረኩም እነዚህን እና ሌሎች ችግሮችን ቀርፎ ኢዜአ በቀጣይ እንዴት መስራት እንዳለበት የሚያሳዩ የተለያዩ ሃሳቦች ተንጸባርቀዋል።

በቀረቡት ጽሁፎች ላይ በተሰጠው አስተያየት በቴክኖሎጂ ተደግፎ ፈጣን የሆነ ዜና ማድረስ እንደሚጠበቅበት አስገንዝበዋል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አቶ በቀለ ሙለታ ከመድረኩ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት፣ ኢዜአ መረጃን በፍጥነት ለደንበኞቹ ለማድረስ ይረዳው ዘንድ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን ሊተገብር መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጠኝ ሚሊዮን ብር የፈጀው ይህ ቴክኖሎጂ በመላው አገሪቱ የሚገኙ ሰላሳ ስድስት የኢዜአን ቅርንጫፎችን ከማዕከል ጋር ከማስተሳሰር ባለፈ ደንበኞች በቀላሉ መረጃ መወሰድ እንዲችሉ እንደሚያግዝም ጠቁመዋል።

የኢዜአ ሰራተኞች ለዚህ በሚመጥን መልኩ ብቁ የሚያደርግ ስልጠና መሰጠቱንም ጠቁመዋል።

ኢዜአ በሶስት መንገድ ማለትም ለአንድ ተቋም ለብቻው፣ ለተወሰኑ ተቋማት በጋራ እንዲሁም ለሁለም ተቋማት በአንድ ላይ ዜና እንደሚያቀርብ የገለጹት አቶ በቀለ በተጨማሪ ኤጀንሲው ተቋማት በሚያቀርቡለት እቅድ መሰረትም ዜና እንደሚያቀርብ ገልጸዋል።

የአንድ ዜና ዝግጅት ማዕከል ላይ ከሆነ እስከ 15ሺህ፣ ወረዳ ድረስ የሚወስድ ከሆነ ደግሞ እስከ 47 ሺህ ብር ወጪ እንደሚደረግበት የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ እነዚህን ዜናዎች ካወጣው ወጪ ከ10 እስከ 15 በመቶ ወጪን በመጋራት ሚዲያዎች መረጃዎቹን መጠቀም እንዲችሉ ከአብዛኛዎቹ ጋር የውል ስምምነት መፈጸሙም ተገልጿል።

ኢዜአ በደንበኞቹ ጥያቄ መሰረት ሙሉ ፊልምና ድምጽ እንደሚያቀርብም አክለዋል።

በሚቀጥለው ዓመት ግንባታው የሚጠናቀቀው ዘመናዊ የሚዲያ ኮንፕሌክስ ግንባታ
የይዘት ስራዎችን በጥራት ለማምረት  የሚያስችልና የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ ታላላቅ ጉባኤዎችን ከአንድ ማዕከል ለማሰራጨት የሚያስችል እንደሚሆንም ዋና ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በዓለም ላይ ከሚገኙ አስር የዜና አገልግሎት ተቋማት ጋር በመረጃ ልውውጥ በቅንጅት እየሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ኤጀንሲው በቀጣይ ነባር ስሙን ሳይቀይር ከአርማው ጀምሮ በሌሎች አገልግሎቶቹ በአዲስ ብራንድ ለመቅረብ ዝግጅት ማጠናቀቁንም አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት "አጃንስ ዳይሬክሲዮን" በሚል መጠሪያ በ1934 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ከተቋቋመ ከ24 ዓመታት በኋላም "የኢትዮጵያ የወሬ ምንጭ" የሚል መጠሪያን አግኝቷል።

በ1960 ዓ.ም ቀዳማዊ ኃይለስላሴ ተቋሙን በጎበኙበት ወቅት ስያሜው እንዲቀየር ባስተላለፉት መመሪያ መሰረት የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሚለውን ስያሜ አግኝቷል።

በአሁኑ ወቅት ተቋሙን እንደ አዲስ ለማቋቋም የሚያስችለው ረቂቅ አዋጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት ታይቶ እንዲጸድቅ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተልኳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም