በምስራቅ ወለጋ ዞን የተራቆተ 72 ሔክታር መሬት በደን ለመሸፈን እየተሰራ ነው

3640

ነቀምቴ  ግንቦት 20/2010 በምስራቅ ወለጋ ዞን የተራቆተ 72 ሔክታር መሬትን በደን ለመሸፈን የሚያስችል ዝግጅት በመካሄድ ላይ መሆኑን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

የጽህፈት ቤቱ የተፈጥሮ ሀብት ልማት እንክብካቤና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ጌታሁን ምናሴ እንዳስታወቁት የተራቆተውን   መሬት በደን ለመሸፈን የ356 ሚሊዮን ችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮ እየተካሔደ ነው፡፡

የችግኝ መትከያ ጉድጓድ ቁፋሮው ካለፈው ሚያዚያ ወር መጨረሻ ጀምሮ በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተካሄደ ሲሆን እስካሁንም 81 ነጥብ 2 ሚሊዮን ጉድጓድ ተቆፍሯል።

ቀሪው እስከ መጪው ሰኔ ወር አጋማሽ ድረስ ይጠናቀቃል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል።

በሚዘጋጀው ጉድጓድ የሚተከለው ችግኝም በዞኑ 17 ወረዳዎች በሚገኙ ችግኝ ማፊያ ጣቢያዎች ተዘጋጅቶ  እንክብካቤ እየተደረገለት እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡

ችግኙ ለአካባቢው ሥነ ምህዳር መጠበቅ አስተዋጽኦ የሚያደርግ፣  የአፈር ለምነትን የሚጨምርና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያለው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ የሳሲጋ ወረዳ የጌላ ቀርሣ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አበራ ለሚ በሰጡት አስተያየት በመጪው ክረምት አንድ ሺህ የግራቪሊያ፣ የሳስባኒያ፣ እና የጀከራንዳ ችግኝ ለመትከል አቅደው በአሁኑ ጊዜ 500 ጉድጓዶችን ማዘጋጀታቸውን ተናግረዋል፡፡

የዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ኤቢዮ ታምሩ በበኩላቸው 500 የተለያየ የዛፍ ችግኝ ለመትከል አቅደው በአሁኑ ጊዜ 200 ጉድጓዶችን ማዘጋጀታቸውንና ቀሪውንም በማዘጋጀት ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በዞኑ ባለፈው ዓመት ከተተከለው 361 ሚሊዮን ችግኝ ውስጥ 71 በመቶው መጽደቁ ከቡድን መሪው ገለፃ ለማወቅ ተችሏል።