የአስተዳደርና ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላት ተሾሙለት

አዲስ አበባ ጥር 28/2011 ለአስተዳደርና ወሰንና ማንነት ጉዳዮች ኮሚሽን አባላትን ለመሾም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጸደቀ።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቅራቢነት የቀረቡት የኮሚሽኑ አባላት በ22 ተቃውሞ፣ በአራት ድምጸ ተዓቅቦ በአብላጫ ድምጽ ምክር ቤቱ አጽድቆታል።

በምክር ቤቱ የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር አቶ ጫላ ለሚ፣ የኮሚሽኑ አባላት ከተለያዩ የሙያ ዘርፍ የተወጣጡ 41 ታዋቂና ሥመ ጥር  ግለሰቦች መሆናቸውን አስረድተዋል።

ግለሰቦቹ በሕግ፣ በታሪክ፣ በሠላምና ደህንነት፣ በፖለቲካ፣ በአንትሮፖሊጂና በጂኦግራፊ የትምህርት መስክ እውቀት ያላቸውና አንዳንዶቹም  መምህራን መሆናቸው ጠቅሰዋል።

በእድሜ ረገድም ከአጼ ኃይለ ሥላሴ ሥርዓተ-መንግሥት  እስከ አሁኑ መንግሥት ረጅም የስራ ልምድ ያላቸው ግለሰቦችም ጭምር መካተታቸውን አብራርተዋል። 

አካባቢን በተመለከተም አራቱንም አቅጣጫ በዳሰሰ መልኩ ግለሰቦቹ መውጣጣታቸውን ጠቁመው የአገር ሽማግሌዎችና የኃይማኖት ምሁራንም እንዳሉበት ተናግረዋል።

የፖለቲካ አመለካከታቸውን ስብጥር ያለው መሆኑን የገለጹት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትሩ የጾታና የአካል ጉዳተኞም ተዋጽዖ ማካተቱን አንስተዋል።

የኮሚሽኑ አባላት ያላቸው ዕውቀትና የሙያ ልምድ በመጠቀም የሚነሱትን የማንነትና የወሰን ጥያቄዎች ለመፍታት እገዛ እንደሚያደርጉ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ግለሰቦቹም ያላቸውን አቅም ተጠቅመው በቁርጠኝነት ለውጤት እንደሚሰሩ መናገራቸውን አቶ ጫላ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አቅራቢነት ለዕርቀ-ሠላም ኮሚሽን አባላት ለማሾም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብም በአብላጫ ድምጽ ጸድቋል።

ለኮሚሽኑ አባልነት የቀረቡት 41 ግለሰቦች በ16 ተቃውሞ፣ በ8 ድምጸ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምጽ ሹመታቸው ጸድቆላቸዋል።

የመንግሥት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትሩ የኮሚሽኑ አባላት በጥንቃቄ ለጉዳዩ ሁነኛ መፍትሄ ለመስጠት ታልሞ የተመለመሉ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ግለሰቦቹም ከተለያዩ የሙያና የህይወት መስመር የተጠሩ መሆናቸውን ጠቁመው ኃላፊነታቸውንም በአግባቡ ለመወጣት  ግለሰቦቹ ቃል መግባታቸውን አስረድተዋል።

በዚህም መሰረት :-
1.ዶ/ር ሙላቱ ተሾመ- የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት
2.ፕሮፌሰር ጥላሁን እንግዳ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
3.ዶ/ር ጣሰው ገብሬ- የቀድሞው የዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት
4.ወ/ሮ መዓዛ ብሩ- ጋዜጠኛ
5.አምባሳደር ሸምሰዲን አህመድ- ዲፕሎማት
6.ዶ/ር ኦባንግ ሜቶ - የሰብዓዊ መብት ተሟጋች
7.ዶ/ር መስፍን አርአያ - በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የህክምና ባለሙያ 
8.ወይዘሮ አማረች አግደው -አማካሪ
9. ኡስታዝ አቡበክር አህመድ - የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ ለውጥ አማካሪ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ
10.ፕ/ር ወልደ አምላክ በእውቀት - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ መምህር 
11.ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳ - ፖለቲከኛና የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዝዳንት 
12.ወይዘሮ ራሔል መኩሪያ - 
13.ዶ/ር ያእቆብ አርሳኖ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 
14. ዶ/ር አረጋዊ በርሔ - ፖለቲከኛ
15.ዶ/ር ደመቀ አጭሶ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 
16.ዶ/ር ካሳሁን ብርሃኑ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 
17. ፕ/ር ገብሩ ታረቀኝ - ፖለቲከኛ
18. ዶ/ር ያዕቆብ ኃ/ማርያም - ፖለቲከኛ
19. ዶ/ር በቀለ ቡላዶ - የቀድሞ ሜይቴክ ዋና ዳይሬክተር
20. አቶ ሌንጮ ለታ - ፖለቲከኛ
21. ፕ/ር መረራ ጉዲና - ፖለቲከኛ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
22. አቶ አንዳርጋቸው ጽጌ - ፖለቲከኛ
23. አቶ ጉደታ ገለልቻ -
24. አቶ አበበ እሸቱ - ፖለቲከኛ
25. ዶ/ር ጳውሎስ ሊቃ - የህክምና ባለሙያ 
26. አቶ ብርሃኑ ተስፋዬ -- የህክምና ባለሙያ 
27. ፕ/ር ፍሥሃጽዮን መንግሥቱ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ
28. ዶ/ር አበራ ደገፉ - መምህር 
29. ፕ/ር በቀለ ጉተማ - ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ 
30. አቶ የሺዋስ አሰፋ - ፖለቲከኛ 
31. አቶ ውብሸት ሙላት - የህግ ባለሙያ 
32. ወ/ሮ ወርቅነሽ ዳባ 
33. አቶ ዘገየ አስፋው 
በእጩነት ከቀረቡት 41 መሃል ስምንቱ በአዲስ ተተክተው የሚከተሉት ግለሰቦች ተካተዋል፡፡
34. ዶ/ር አሸብር ወ/ጊዮርጊስ
35. ዶ/ር / ዳዊት መኮንን
36. አቶ ባዩ በዛብህ
37. አቶ በለጠ ሞላ
38. አቶ ዮናስ ዘውዴ
39. አብዱልባሲጥ ምንዳዳ
40. አብዱራሂም መሐመድ
41.ዶ/ር በላይ ንጉሴም

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም