የአማራ የባህል ስፖርት ውድድር በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የዝግጅት ሥራ ተጠናቋል

826

ሰቆጣ ጥር 26/2011 በሰቆጣ ከተማ ከነገ ጀምሮ የሚካሄደው 16ኛው የአማራ የባህል ስፖርት ውድድር በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ የዝግጅት ሥራው መጠናቀቁ ተገለፀ፡፡

በሰቆጣ ከተማ ለሚካሄደው 16ኛው የአማራ የባህል ስፖርት ውድድር ከጥር 27 እስከ የካቲት 6 ቀን 2011 ዓ.ም ድረስ እንደሚካሄድ  የክልሉ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን አስታውቋል፡፡

የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት አቶ አለምነው ሁነኛው ለኢዜአ እንደገለፁት በየአመቱ ለሚካሄደው የባህል ስፖርት ውድድር 11 ዞኖችና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ተሳታፊ የሚሆኑ ሲሆን ለውድድሩም የቅድመ ዝግጅት ሥራው ተጠናቋል፡፡

ምስራቅ ጎጃም፣ ምዕራብ ጎንደር እና ደሴ ከተማዎች በበጀት እጥረት ምክንያት ዘንድሮ እንደማይሳተፉም ጠቁመዋል፡፡

“ገና፣ ገበጣ እና ትግልን ጨምሮ በ11 የባህል ስፖርት አይነቶች ውድድሩ ይካሄዳል” ብለዋል፡፡

በአዘጋጁ ዋግ ኽምራ ዞን የፈረስ እጥረት በመኖሩ የፈረስ ሽርጥና ጉግስ ውድድሮች በሰሜን ወሎ ዞን መቄት ወረዳ  እንደሚካሄዱም አመልክተዋል፡፡

በዘንድሮ የባህል ስፖርት ውድድር የህብረተሰቡን ተሳትፎ ከማሳደግ ባሻገር በክልሉ የሚገኙ ብሄረሰቦች ወግ፣ ልምድና ቋንቋቸውን የሚያንፀባርቁበት የባህል ትርኢት  መድረክ እንደሚዘጋጅ  ፕሬዚዳንቱ ገልጸዋል፡፡

የብሄረሰብ አስተዳደሩ ስፖርት ኮሚሽን ኃላፊ አቶ አዲሴ በላይ በበኩላቸው እንዳሉት የ16ኛውን የአማራ የባህል ስፖርት ውድድር በሰቆጣ ከተማ እንዲካሄድ መደረጉ የብሄረሰብ አስተዳደሩን ባህልና ቋንቋ ለማስተዋወቅ ጠቀሜታ አለው።

“ከእዚህ ባለፈ ለነጋዴው ማህበረሰብ የኢኮኖሚ መነቃቃት ለመፍጠር ጉልህ ሚና ይጫወታል” ብለዋል፡፡

ስፖርተኞች በውድድሩ ቆይታቸው ያማረ እንዲሆን በከተማው የአልጋ፣ የምግብ፣ የህክምና እና ለጸጥታ ስራዎች ቅድመ ዝግጅት ተደርጓል፡፡

በ16 ኛው የአማራ ባህል ስፖርት ውድድር ከ800 በላይ ስፖርተኞች እንደሚሳተፉ ከክልሉ የባህል ስፖርት ፌዴሬሽን አየተገኘ መረጃ ያመላክታል፡፡