ከዘርና ከማንነት ጋር የተያያዙ የእግር ኳስ ክለቦች መመሰርታቸው የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሩን አብሶታል ተባለ

981

አዲስ አበባ ጥር 26/2011 ከዘርና ከማንነት ጋር የተያያዙ የእግር ኳስ ክለቦች መመስረታቸው ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል አንድ ምክንያት ሆኗል ተባለ።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የክለብ አመራሮች እንዳሉት፤  የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ጎልቶ የወጣው ክለቦች ከዘርና ማንነት ጋር በተያያዘ ስያሜ በመመስረታቸው ነው።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የቦርድ ሊቀመንበር አቶ አብነት ገብረመስቀል በኢትዮጵያ እግር ኳስ ዙሪያ በሚታዩ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ላይ በርካታ ምክንያቶች ቢኖሩም ጎልቶ የሚነሳው “ክለቦች ከዘርና ማንነት” ጋር ስያሜ ይዘው መመስረታቸው  ነው ብለዋል።

እግር ኳስን ከዘርና ፖለቲካ መቀላቀል መጥፎ ስሜት ውስጥ እንደሚከት ገልጸው፤ ደጋፊዎች ክለባቸው ሲሸነፍ “ማንነታችን ተነካ”  የሚል ስሜት ውስጥ በመግባት ችግር እፈጠሩ መሆኑን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ በ1950 ዎቹ ተመሳሳይ ሁኔታ ተከስቶ እንደነበር ያስታወሱት አቶ አብነት በወቅቱ ችግሩ የተፈታው ከዘርና ከማንነት ጋር የተገናኘ ስያሜ ያላቸውን ክለቦች በድርጅት ስም እንዲቀይሩ በመደረጉ እንደነበር ገልጸዋል።

የአዳማ ከተማ እግር ኳስ ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አንበሴ መገርሳ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የሚታየው ከስፖርቱ ውጭ የተለየ ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች የእግር ኳስ ሜዳዎችን እንደ ምቹ አጋጣሚ ለመጠቀም በማሰባቸው ነው።

የክለብ እግር ኳስ አመራሮች ችግሩን ለመቆጣጠር ትልቁን ድርሻ ወስደው ኃላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

የኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን ስፖርት ክለብ ስራ አስኪያጅ አቶ አሸናፊ እጅጉ የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሮች ከስፖርት ባህሪ ይልቅ የማንነት ማሳያ እየሆኑ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

የስፖርታዊ ጨዋነት ችግሩን ከስሩ ለመፍታት ከላይ ከተነሱት በተጨማሪ ሁሉም ስፖርት ወዳድ ዜጋ ሀላፊነት ተሰምቶት መስራት እንደሚጠበቅበት የክለብ አመራሮቹ ጠቁመዋል።

ከቅርብ አመታት ወዲህ በእግር ኳስ ሜዳ ላይ በሚፈጠር የስፖርታዊ ጨዋነት ችግር የተነሳ ከፍተኛ የሆነ ጉዳት እየደረሰ ነው።

በሜዳ ላይ በሚፈጠር ችግር የተነሳ በሰዎችና በንብረት ላይ ጉዳት ሲደርስ እየተስተዋለ ነው።

—END—