ለቱሪዝም ልማት የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ ይገባል

1143

ደብረ ማርቆስ ጥር 26/2011 ባህላዊና ተፈጥሯዊ እሴቶችን በመጠበቅና በማስተዋወቅ የቱሪዝም ልማቱን ማሳደግ እንዲቻል የመገናኛ ብዙሀን ትኩረት ሰጥተው ሊሰሩ እንደሚገባ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴር መስሪያቤቱ በምስራቅ ጎጃም ዞን የሚገኙ ታሪካዊ እና ሃይማኖታዊ የቱሪስት መዳረሻ ቦታዎችን ከጥር 18 ጀምሮ ለመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ያዘጋጀው የማስጎብኘት መርሀግብር ትናንት ተጠናቋል።

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የህዝብና ዓለምአቀፍ ግንኙነት ዳሬክተር አቶ ገዛኽኝ አባተ ለኢትዮዽያ ዜና አገልገሎት እንደተናገሩት የሀገሪቱ ባህላዊ፣ ሃይማኖታዊና  እና ተፈሮአዊ እሴቶች በሚገባ ታውቀውና ተጠብቀው የቱሪዝም ልማቱን ማሳደግ እንዲቻል መገናኛ ብዙኃን በትኩረት ሊሰሩ ይገባል።

ጉብኝቱ የአካባቢው ባህላዊ እና ተፈጥሮአዊ እሴቶች እንዲተዋወቁ፣ እንዲለሙ፣ ተጠብቀው ለተተኪው ትውልድ እንዲተላለፉና በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እንዲፈጠር የማድረግ ዓላማ እንዳለውም ጠቁመዋል።

አቶ ገዛኽኝ አንዳሉት የመገናኛ ብዙሀን ባለሙያዎች የቱሪስት መስህቦችን እራሳቸው አወቀው ለሀገር ውስጥም ሆነ ለውጭ አገር ቱሪስት እንዲያስተዋውቁ ለማስቻል በሀገር አቀፍ ደረጃ የባህልና ቱሪዝም የሚዲያ ፎረም ተቋቁሟል።

የሚዲያ ፈረሙ አስተባበሪ ጋዜጠኛ ዘሪሁን ግርማ በበኩሉ የቱሪዝም ሀብቱን ለማስተዋወቅ  በመንግስት ከሚሰራው ስራ በተጓዳኝ ፎረሙ ዘርፉን የማስተዋወቅ ሥራ መጀመሩን ተናግሯል።

በቱሪዝም ዘርፉ ለዘገባ በተሰማሩ እና ለፎረሙ አባል ጋዜጠኞች ስልጠናዎችን በመስጠት ፎረሙን የማጠናከር ሥራ እንደሚሰራም አመልክቷል።

ከጉብኝቱ ተሳታፊዎች መካከል የኢቢኤስ ቴሌቭዥን ባልደረባ ጋዜጠኛ ፍስሀ ደሳለኝ  “ጉብኝቱ በአካባቢው ያለውን የቱሪዝም ሀብት ከዚህ በፊት እሰማው ከነበረው የበለጠ በአይኔ አይቼ  እንድረዳ  አድርጎኛል” ብሏል።

በአካባቢው የተመለከታቸውን የቱሪዝም ሀብቶች ለማስተዋወቅና በቱሪስቶች እንዲጎበኙ ለማድረግ የድርሻውን እንደሚወጣ ገልጿል።

የዳሽን ሚዲያ ኮሚኒኬሽን ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘመነ ዮሐንስ በበኩላቸው  የማህበረሰቡ እንግዳ አቀባበል የኢትዮጵያዊነትን ባህል ያለቀቀ መሆኑ ከጉብኝቱም በላይ እንዳስደሰተው ተናግሯል።

በዞኑ በተካሄደው የጉብኝት መርሀግብር ከ20 በላይ የመገናኛ ብዙሃን የተወከሉ ባለሙያዎችን ጨምሮ ከፌደራል እስከወረዳ የሚገኙ የባህልና ቱሪዝም በላሙያዎች መሳተፋቸው ታውቋል።