ነገን ዛሬ እንስራ

1174

ሰለሞን ተሰራ/ኢዜአ/

ወጣትነት ለሥራ፣ ለትግል፣ ለለውጥ፣ ለአዲስ ነገር ተነሳሽነት ጎልቶ የሚታይበት ዕድሜ እንደመሆኑ፣ የአንዲት አገር ዕድገት፣ ለውጥና መሻሻል ወይም ለዚህ ተቃራኒ ውጤት በየዘመኑ ባለው የወጣት ትውልድ እንቅስቃሴ የሚወሰን መሆኑ ዕውነት ነው።

በኢትዮጵያ አሁን ለመጣው ለውጥ ወጣቱ አስተዋፅኦ ማበርከቱን ብዙዎች ይስማሙበታል። በኢትዮጵያ ከ2008 ዓ.ም. ጀምሮ በወጣቶች ጥያቄ ተቀስቅሶ በነበረው አገራዊ አመፅ፣ ተቃውሞና ሁከት ወጣቶች ዋነኛ መሣሪያ እንደነበሩ መንግሥት በተደጋጋሚ ሲናገር ተደምጧል፡፡

በኦሮሚያና በአማራ ክልል በተነሳው ተቃዉሞ ወጣቶችን በስፋት ተሳታፊ ሆነው የመልካም አስተዳደር በደልን በጽኑ ተቃውመው አገሪቱ የለውጥ መስመር እንድትይዝ ጥርጊያ መንገድ አበጅተዋል። የዚህ ለውጥ ምንጭ የኢትዮጵያ መንግስት «እድገቱ በራሱ የፈጠራቸዉ አዳዲስ ፍላጎቶች እና አስቀድሞ በወጉ ያልተቀረፉ ችግሮች ተዳምረዉ አሁንም የወጣቶቹን ፍላጎት በሚፈለገዉ ደረጃ ማርካት አልተቻለም» የሚል አቋም ይዟል።

የወጣቶች የልማትና ተጠቃሚነት ፓኬጅ የተቀረፀ ቢሆንም የወጣቶችን የልማት ፖሊሲ አስፈጻሚ ተቋም በፌዴራልና በክልል መንግሥታት ካቢኔ ውስጥ ተዋቅሮ እስከ ታችኛው ድረስ የመንግሥት አስተዳደር መዋቅር ቢዘረጋም የሚፈለገውን ያህል ሰኬታማ ሥራ አልተከናወነም።

ሥራ ፍለጋ ከገጠር ወደትናንሽ ከተሞች የሚፈልሱ እንዲሁም ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርሲቲ ሁለተኛ ዲግሪ እንዲሁም በተለያያ ደረጃ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት ተመርቀው የሚወጡ ወጣቶችን ማስተናገድ የሚችል የሥራ እድል ስላልተፈጠረ ከተሞች የሥራ አጥ መናኸሪያዎች ሆነዋል።

የአገሪቱን ከተሞች ያጨናነቁ ከዓመት ዓመት ቁጥራቸው እየጨመረ የሚሄድ ሥራ ፈላጊ ወጣቶች የተስፋ መቁረጥ ስሜት አድሮባቸዋል። በአገራቸው ሥራ አግኝተው የተሻለ ህይወት የመኖር ተስፋ የራቃቸው ወጣቶች ለህገ ወጥ የሰዎች ዝውውርና ስደት ተጋልጠዋል።

በአገራቸው ምንም የሚጨበጥ ነገር ያጡ ወጣቶች በህገ ወጥ መንገድ ለመሰደድ ሲነሱ ከችግሩ በስተቀር ምንም የሚያጡት ነገር እንደሌለ ስለሚሰማቸው ህገ ወጥ ስደት ሊያስከትል የሚችለው አደጋ ብዙም አያሳስባቸውም።

ኢትዮጵያ ሰፊ ቁጥር የያዘውን ወጣት ትውልድ በስራ ፈጠራ በመታገዝ ከችግርና ድህነት ማላቀቅ ካልቻለች በቅርቡ የተጋፈጠችው አይነት ፖለቲካዊ ቀውሶች ላለመደገማቸው ዋስትና ማስቀመጥ አዳጋች መሆኑን ባለሙያዎች ይጠቅሳሉ።

ፕሮፌሰር አለማየሁ ገብረማሪያም “አቦሸማኔው ትውልድ” በሚለው የእንግሊዝኛ ጽሁፋቸው ውስጥ እንዳስቀመጡት በአገሪቱ ከፍተኛውን ቁጥር የሚይዘው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ወደስራ እንዲገባ የሚያስችለው እድል ሊፈጠርለት እንደሚገባ ያመለክታሉ።

በ2011 የወጣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) የልማት ፕሮግራም ሪፖርት እንደሚያመለክተው 77.8 በመቶ የሚሆነው የኢትዮጵያ ወጣት ኑሮውን የሚገፋው በቀን ከሁለት የአሜሪካን ዶላር ባነሰ የገንዘብ መጠን ነው።

አገሪቱ 100 ሚሊዮን ከሚገመተው ህዝቧ ውስጥ እስከ 70 በመቶው ወጣት ወይም ከ 30 አመት እድሜ በታች የሆነ ህዝብ መሆኑ ይነገራል፡፡ በዚህ የተነሳ ኢትዮጵያ ለወጣቶች የስራ እድል በመፍጠር ላይ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ አለባት ነው የተባለው፡፡

መቀመጫዉን ለንደን ያደረገዉ የብሪታኒያዉ አጥኚ ተቋም ‘ቻተም ሃዉስ’ የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ፖሊሲ የወጣቱን ጥም ማርካት እንዳልቻለ ይተቻል።

በተቋሙ አጥኝ የሆኑት ጄሰን ሞስሊ በኢትዮጵያ በየዓመቱ 600 ሺህ ወጣቶች ስራ ፈላጊዉን ማሕበረሰብ እንደሚቀላቀሉ በፅሁፋቸዉ ጠቅሰዋል። መንግስት ባለፉት አስር ዓመታት ሐገሪቱ ስላስመዘገበችዉ የኢኮኖሚ ዕድገት በሰፊዉ የሚናገረዉ በተጨባጭ ካለዉ የስራ እድል እዉነታ ጋር አለመጣጣሙ ለወጣቱ ትዉልድ ብዥታ መፍጠሩን ያብራራሉ። ይሕም በወጣቱ ዘንድ ቅሬታን ኋላም ቁጣን ማስከተሉን ገልፀዋል።

የልማታዊ ኢኮኖሚክስ ምሁርና ከፍተኛ የጥናት ባለሙያ ሶስና በዙ በ’ዘ ኮንቨርሴሽን’ ላይ ያሰፈሩትን አንድ ትንታኔ ዋቢ ያደረገው የ’ሜል ኤንድ ጋርዲያን አፍሪካ’ ዘገባ ኢትዮጵያ ወጣቱን ትውልድ ከፖለቲካ ችግር አላቆ የልማት ኃይል ለማድረግ ሰፊ እድል እንዳላት ያትታል፡፡ አገሪቱ ለወጣቶቿ የስራ እድል በመፍጠር ከድህነትና ችግር ለማላቀቅ እስከሰራች ድረስ ከኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ባለፈም ዘላቂ የጸጥታና ሰላም ዋስትናም ታገኛለች ነው የተባለው፡፡

ይሁን እንጂ መንግስት ይህን ሰፊ ቁጥር ያለው ወጣት  ጥያቄና ተጠቃሚነት መመለስ የማይችል ፖሊሲን የሚከተል ከሆነ አገሪቱ ኢኮኖሚዋም ሆነ ሰላሟ ይናጋል ሲል ነው ዘገባው አጠንክሮ የገለጸው፡፡

ቻይናና ደቡብ እስያ ከ 50 አመት በፊት በነበሩበት ሁኔታ ላይ ኢትዮጵያ እንደምትገኝ እንደማነጻጸሪያ ያነሳው ዘገባው እነዚህ አገሮች ወጣቱና አምራቹን ህዝባቸውን በሰፊው በመጠቀም ትልቅ የኢኮኖሚ ስኬት ማግኘታቸውን ያስረዳል፡፡

በቅርብ ጊዜያት በኢትዮጵያ መንግስትን የተቃወመው ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ቁጥሩ ብዙ መሆኑን ያወሳው ዘገባው ይህ ደግሞ የመጣው ከድህነትና ስራ አጥነት ነው ሲል ያስቀምጣል፡፡ መንግስት በድህነት ውስጥ ላለው ለዚህ የህብረተሰብ ክፍል የስራ እድል በመፍጠር አገሪቱ በኢኮኖሚና በጸጥታው በኩል ተጠቃሚ እንድትሆን ማድረግ ይችላል ይላል ዘገባው፡፡ በዚህ የተነሳ መንግስት የቀደመውን መንገድ ቀይሮ ለወጣቱ ስራ ይፍጠር ሲል ዘገባው ይመክራል።

አገሪቱ ባለፉት ሁለት አመታት ገጥመዋት የነበሩትን ቀውሶች በማራገፍ ወጣቱን ተጠቃሚ ለማድረግ መሪዎቿና ህዝቦቿ በአንድ ልብ ሆነው መንቀሳቀስ መጀመራቸው እየታየ ነው። የወጣቶች ጥያቄ በአግባቡ ባለመመለሱ ህዝቡን ለብሶት መዳረጉ ከግምት ውስጥ ገብቶ ወጣቱን በብቃት ማሳተፍ ያስፈልጋል። ”ያለወጣቶች ተሳትፎ የታለመውን እድገት ማሳካት አይቻልም” ብለው ወደፊት በወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ላይ ጠንክሮ በመስራት ለለውጥ መዘጋጀት እንደሚገባም ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በበዓለ ሲመታቸው ወቅትና በተለያዩ ወቅቶች መናገራቸው ይታወቃል።

በተለይም  እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ባላቸው አገራት የሚኖሩ ወጣቶች በሰላምና በዕድገት ጎዳና ለመዝለቅ  እርስ በርስ ተከባብሮና ተቻችሎ መኖር አማራጭ ሳይሆን ግዴታቸው ነው፡፡ በማህበራዊ ሚዲያዎች የሚሰራጩ የዘረኝነት ስድቦች፣ የባህል ወረራ፣ ሃይማኖታዊ ትንኮሳዎችና የውሸት ፖለቲካ  በተለይ ወጣቶች ተረጋግተው የዕለት ተዕለት ስራቸውን እንዳያከናውኑ በማድረግ በግንባር ቀደም የሚጠቀሱ ናቸው፡፡

ይህ ደግሞ ወጣቱ ማሕበረሰቡ በሰላምና በፍቅር ተሳስቦ የሚኖርበትን ባሕል ከማጠናከር ይልቅ ጥላቻን እያስፋፋ ይገኛል፡፡ ወጣቱም ይህንኑ ማህበራዊ ቀውስ በመከላከል ዘርፉን ለበጎ አላማ በማዋል አገሩን ወደፊት የማራመድ ኃላፊነት እንዳለበት ሊገነዘብ ይገባል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ”ወጣትነት የእሳት ጊዜ ነው፣ ወጣትነት ውስጥ በእርግጥም፣ እሳትነት እና ከባድ ግለት አለ ይህን እሳት፣ ብረት አቅልጡበት፤ ወንዝ ጥለፉበት፤ ተራራ ናዱበት” በማለት ያስተላለፉትን መልእክት በመከተል ለአገሪቱ ሁለንተናዊ ለውጥ በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል የሚኖረው ወጣት በጋራ መሰለፍ አለበት።