የቂርቆስና የአዲስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች ድጋፍ አደረጉ

84

ባህር ዳር  ጥር 26/2011 በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የቂርቆስና የአዲስ ክፍለ ከተማ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቀለው በአማራ ክልል የተለያዩ መጠለያዎች ለሚገኙ ወገኖች ከ2 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያለው የቁሳቁስ ድጋፍ አደረጉ።

የክፍለ ከተሞቹ ነዋሪዎች ተወካዮች ያሰባሰቧቸውን ቁሳቁሶች ዛሬ በባህር ዳር ከተማ ተገኝተው ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስረክበዋል።

የቂርቆስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ የትናየት ሙሉጌታ በርክክቡ ስነ ስርዓቱ ላይ  እንደገለጹት "የቁሳቁስ ድጋፉን ያደረግነው የአማራ ክልል ተወላጆች ከተፈናቃዮች ጎን መሆናችንን በተግባር ለማሳየት ነው" ብለዋል።

ድጋፉም ከ1 ነጥብ 8 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው ሦስት ሺህ 500 ብርድ ልብሶች፣ አንሶላዎች፣ ፍራሾችና ሌሎች ቁሳቁሶችን መለገሳቸውን ገልጸዋል።  

ቁሳቁሶችን ያሰባሰቡት በክፍለ ከተማው ከሚኖሩ የአማራ ክልል ተወላጆች፣ የልማት አጋሮችና በከተማዋ ከሚኖሩ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች መሆኑንም አመልክተዋል።

የአዲስ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ኤፍሬም አድማሱ በበኩላቸው ግምታቸው ከ360 ሺህ ብር በላይ የሚሆኑ 271 ፍራሾችና ሌሎች አልባሳትን ከነዋሪዎችና ከልማት አጋሮች በማሰባሰብ ይዘው መምጣታቸውን ተናግረዋል።

ተፈናቃዮችን መልሶ ለማቋቋም በሚደረገው ጥረት የክፍለ ከተማው ነዋሪዎች ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉም አመልክተዋል። 

የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባበሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ አማረ ክንዴ በርክክቡ ወቅት እንዳሉት ለተፈናቃዮቹ  በፌዴራልና በክልሉ መንግስት እየተደረገ ያለው የዕለት እርዳታና ድጋፍ ሳይቆራረጥ እንዲደርስ በትኩረት እየተሰራ ነው።

መንግስት ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ ህብረተሰቡ የመረዳዳት ባህሉን ተጠቅሞ ለተፈናቃዮች የተለያዩ የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆኑንም ተናግረዋል።

በአዲስ አበባ ቂርቆስና አዲስ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ ቅን አሳቢ የህብረተሰብ ክፍሎች ያደረጉት የቁሳቁስ ድጋፍ ለተፈናቃዮቹ እንደሚደርስ ቃል ገብተዋል።።

አቶ አማረ እንዳሉት የክልሉ መንግስት 36 ሚሊዮን ብር በመመደብ የፌዴራል መንግስት በማይደርስባቸው አካባቢዎች ጭምር ለመድረስ እየሰራ ነው።

በተለያዩ ክልሎችና በክልሉ ውስጥ በተፈጠሩ ግጭቶች ከ60 ሺህ የሚበልጡ ተፈናቃዮች በክልሉ በሚገኙ ወረዳዎችና ከተማ አስተዳደሮች በተዘጋጁ 13 መጠለያ ጣቢያዎች ተጠልለው እንደሚገኙ ታውቋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም