የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ እያደረገ መሆኑን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ

53

ጎንደር ጥር 26/2011 የሥጋ ደዌ ተጠቂዎችን በኢኮኖሚ ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን የሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የስጋ ደዌ ቀን በአገር አቀፍ ደረጃ ለ20ኛ ጊዜ በጎንደር ከተማ በተለያዩ ዝግጅቶች ትናንት መከበር ጀምሯል።

በበዓሉ መክፈቻ ስነስርዓት ላይ የተገኙት የሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ጌታሁን አብዲሳ የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን አስታውቀዋል።

በስጋ ደዌ ተጠቂዎች ላይ ቀደም ሲል ይደርስ የነበረው በደልና መገለል በአሁኑ ወቅት ተለውጧል ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው በእዚህም ብዙዎቹ ከጥገኝነት ተላቀው የራሳቸውን ህይወት መምራት እንደቻሉ ተናግረዋል።

የስጋ ደዌ ተጠቂዎች በየደረጃው በሚገኙ ማህበራት ታግዘው እራሳቸውን በኢኮኖሚ ለማቋቋም የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

አቶ ጌታሁን እንዳሉት መንግስት ከአገር ውስጥና ከውጪ አገራት ለጋሾች ጋር በመተባበር ለስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማህበራት የብድር፣ የማምረቻና የመስሪያ ቦታዎችን ከማመቻቸት ጀምሮ የሙያ ባለቤት የሚሆኑበትን ስልጠና እንዲያገኙ ጥረት አድርጓል።

"የአማራ ክልል የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን በማቋቋም በኩል እያደረገ ያለው ጥረት ለሌሎች ክልሎችም ምሳሌ ሊሆን የሚችል ተግባር ነው" ብለዋል።

የኢትዮጵያ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ብሔራዊ ማህበር ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ታደሰ በበኩላቸው ብሔራዊ ማህበሩ በአገሪቱ ሰባት ክልሎች 20 ሺህ አባላት ያቀፉ 70 ማህበራትን እንዲቋቋሙ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡

የስጋ ደዌ ተጠቂዎችን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥም ብሔራዊ ማህበሩ ከአጋር አካላት ጋር በመቀናጀት አባላቱ የብድር አገልግሎት አግኝተው ከልመናና ከተመጽዋችነት እንዲላቀቁ እያደረገ መሆኑንን አስረድተዋል።

የጎንደር ከተማ ምክትል ከንቲባ ዶክተር ሙሉቀን አዳነ በበኩላቸው ብሔራዊ በዓሉ በአገር አቀፍ ደረጃ በጎንደር ከተማ መከበሩ ህብረተሰቡ ለስጋ ደዌ ህሙማን የሚያደርገውን ድጋፍና ትብብር ለማጠናከር የሚያግዝ መሆኑን አመልክተዋል።

በወተት ላሞች እርባታ፣ በማገዶ ቆጣቢ ምድጃና በብሎኬት ማምረት እንዲሁም በወፍጮ አገልግሎት የተሰማራው የጎንደር ከተማ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ማህበር የሥራ እንቅስቃሴ በበዓሉ እንግዶቹ ተጎብኝቷል፡፡

በዓሉን ምክንያት በማድረግም በትናንትናው ዕለት የእግር ጉዞና የአካል ጉዳተኞች የአጭር ርቀት የሩጫ ውድድር የተካሄደ ሲሆን በዛሬው መርሃ ግብርም ከአገር አቀፍ፣ ከክልል፣ ከዞንና ከወረዳዎች በተጋበዙ ተሳታፊዎች የፓናል ውይይት እየተካሄደ ነው።

የዘንድሮ የስጋ ደዌ ተጠቂዎች ቀን በዓል እየተከበረ ያለው "የስጋ ደዌ ስርጭትን በመግታትና ተጠቂዎችን በማብቃት አካታችነትና እኩልነትን እናረጋግጣለን" በሚል መሪ ቃል ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም