የአዲስ አበባ የመሬት ልማት ቢሮ አገልግሎት አሰጣጥ መሻሻሎች ቢያሳይም በታችኛው መዋቅር የተቀናጀ አሰራር አይታይም … ተገልጋዮች

83

ጥር 26/2011 በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ቢሮ አገልግሎት አሰጣት ላይ  መሻሻሎች ቢኖሩም እስከ ወረዳ ድረስ የተቀናጀ  አሰራር  እንደማይታይ ተነገረ፡፡

የተቋሙ ተገልጋዮች ለኢዜአ  በሰጡት አስተያየት አንድን ጉዳይ ለማስፈፀም ካሁን በፊት የነበረው መመላለስና መጉላላት ሙሉ ለሙሉ አልተቀረፈም፡፡

የግንባታ ፈቃድ ለመጠየቅ ወደ ቢሮው የመጡት አቶ ደሳለኝ መኩርያ  በሰጡት አስተያየት “አገልግሎት አሰጣጣቸው  የተጓጓተተ ነው ማለት እችላለሁ፤ መመላለስ ከጀመርኩ ወደ አምስት ወር ሆኖኛል ፤ሃላፊው የለም፣ጉዳይህ የያዘው ባለሞያ ስልጠና ላይ ነው፣ መብራት የለም ፣ሲሰተም የለም ከሚሰጡን ምክንያቶች ጥቂቶቹ ናቸው” ብለዋል፡፡

በቢሮ ደረጃ የሰራተኞቹ አገልግሎት አሰጣጥ በመሻሻሉ አሁን ላይ ስልጣንን ተገን አድረጎ ተገልጋይን ማመናጨቅ አይታይም ጥሩ ቢሆኑም በበዓላት ማግስት ለሁለትና ሶስት ቀናት ሰራተኞቹ በቢሮ ያለመገኘት ና  የተቀናጀ አሰራር ከወረዳ እስከ ቢሮ ያሉ የቅንጅት መጓደል  መስተካከል አለበት ነው ያሉት፡፡

ስማቸው መግለፅ ያልፈለጉ ሌላው ተገልጋይ በበኩላቸው "ይዞታህ ከመቃብር ስፍራ ጋር ተካቶ የተያዘ ስለነበረ መፍትሄ ፍለጋ ወደ ፕላን ኮሚሽን ሄጄ ስጠይቅ ጥናት ተደርጎ ለአረንጓዴ ልማት ተከልሏል ይሉኛል ግሪን ኤርያ ጋር ሄጄ ስጠይቅ የኛ አይደለም ይሉኛል ሰነዱ ላይ ያለው ነገር  ለመቃብር ስፍራ እንደተሰጠ ያመለክታል" በሚል መፍትሄ እንዳላገኙ ተናግረዋል ፡፡

በሚነግሩኝ ሁለት የሚቃረኑ  ምክንያቶች ትክክለኛው ለመለየት እና በይዞታዬ ላይ ልማት መስራት ባለመቻሌ መፍትሄ እንዲሰጠኝ ብመጣም አላስተናገዱኝብ  ነው ያሉት፡፡

የተቋሙ ተገቢና ፈጣን ምላሽ መስጠት የሚችል አቅም እንዲኖረው በሰው ሃይል ማደራጀት እንደሚያስፈልግ አስረድተዋል፡፡

 ሼህ ኢብሳ መሐመድ  የተባሉ ተገልጋይ  በበኩላቸው አገልግሎት አሰጣጥና አቀባበል ላይ የተሻለ ነገር እንደሚታይና ፤ቀደም ሲል የተወሳሰቡ ነገሮች አሰራሮች አሁን ላይ መሻሻል  እንደሚታይ ተናግረዋል፡፡

“መመሪያቸው ላይ ግልፀኝነት ይኑረው፤ አሁንም ብዙ ነገሮች ይቀራሉ  ተገልጋይ አላሰፈላጊ መጉላላት አለ” ብለዋል፡፡    

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሬት ይዞታ አስተዳደር ፅህፈት ቤት ስራ አስኪያጅ  አቶ ዘሪሁን ቢቂላ በቀረቡት ቅሬታዎች ላይ በሰጡት ምላሽ በወረዳዎችና በክፍለ ከተሞች ያለው የመልካም አስተዳደርና የኪራይ ሰብሳቢነት ችግርን ለመቅረፍ አየተወሰዱ ያሉ የአመራር ለውጥና የህግ እርም መሻሻሎች  ቢኖሩም ችግሮቹ በሚፈለገው ደረጃእንዳልተቀረፉ  አስታውቀዋል፡፡

በአገልግሎት ስጪዎች በኩልም ውሳኔ የሚያሰፈልጋቸው ጉዳዮች ሲያጋጥሙ ተጠያቂነት በመፍራት  ውሳኔ ያለመስጠት  ችግር መኖሩንም ጠቅሰዋል፡፡ 

በተገልጋዩ ሕብረተሰብ በኩልም መብቱን ጠንቅቆ ካለማወቅ እና አስፈላጊውን ማስረጃ ይዞ ካለመገኘት የተነሳ ለስራው መጓተት ድርሻ እንዳለው የተቋሙ ኃላፊው አንስተዋል፡፡

አቶ ዘሪሁን እንዳሉት የአገልግሎት አሰጣጡን ለማሻሻልና ኪራይ ሰብሳቢነት ለማስቀረት የሚያግዝ በቴክኖሎጂ የተደገፈ አሰራር ለመተግበር በዝግጅት ላይ እንደሆኑም ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል ፡፡

ቴክኖሎጂው በተወሰኑ ቦታዎችም በሙከራ ደረጃ በመተግበር ላይ እንደሚገኝና እስከቀጣዩ አመት ይፋ እንደሚደረግ ጠቁመዋል፡፡

አዲሱ ቴክኖሎጂ ሕብረተሰቡ ጉዳዩ ለማሰፈፀም በመመላለስ የሚያጠፋውን ጊዜና ጉልበት በመቆጠብ በቤቱ ሆኖ የሚፈልገውን መረጃ በማግኘት ጉዳዩን የሚከታተልበት እድል ይፈጥርለታል ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም