ችግሮችን በሰለጠነ መልኩ የመፍታት ባህል መዳበር አለበት… ጽህፈት ቤቱ

72
አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2010 የኢትዮጵያ ተሰሚነትና መልካም ገጽታ በዓለም እንዲጎላ ውስጣዊ ችግሮችን በሰለጠነ መልኩ የመፍታት ባህል መዳበር እንደሚገባው  የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት አስታወቀ። ጽህፈት ቤቱ 'ውስጣዊ ጥንካሬያችን ለውጫዊ ገጽታችን መቀየር ጽኑ መሰረት ነው' በሚል ርዕስ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በላከው መግለጫ እንዳመለከተው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ሰሞኑን በጂቡቲ እና ሱዳን ያደረጉት ጉብኝት ስኬታማ ነበር። ኢትዮጵያ ከሁሉም ጎረቤት አገራት ጋር በመልካም ጉርብትና፣ በትብብርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት የማራመድ ፖሊሲዋን እንደምትቀጥልም ገልጿል። ከሰሞኑ የተለያዩ አገራት መሪዎች ለጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ መምጣታቸውንና ወደ አገሪቱ የሚመጣው ቀጥተኛ የውጭ ኢንቨስትመንት ፍሰት መቀጠሉንም አውስቷል። የሥራ ጉብኝቶች የሚያረጋግጡት በአስቸጋሪ ወቅት እንኳን አገሪቱ በሰላም፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በሌሎችም ዘርፎች ተፈላጊነቷ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው ይላል መግለጫው፡፡ የነዚህ ሁሉ ተፈላጊነት ምስጢር በውስጥ የተፈጠረው ጥንካሬ ነውና ውስጣዊ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ በመፍታት፤ ዴሞክራሲያዊ አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አመልክቷል። ህዝቡ በአገሪቱ የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ከዳር ለማድረስና የአገሪቱን በጎ ገጽታ ለመገንባት እንዲረባረብም ጽህፈት ቤቱ ጥሪ አቅርቧል፡፡ በኢፌዴሪ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽ/ቤት የተዘጋጀ ሳምንታዊ አቋም መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል ውስጣዊ ጥንካሬያችን ለውጫዊ ገጽታችን መቀየር ጽኑ መሰረት ነው ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ  አህመድ ሰሞኑን ጂቡቲን እና ሱዳንን ጎብኝተው ተመልሰዋል። የሥራ ጉብኝታቸው ከሁለቱ ጎረቤት አገራት ጋር ያለንን መልካም ግንኙነት፣ የጋራ ተጠቃሚነት እና ትስስርን ለማጠናከር ያለመ ነበር። እንደሚታወቀው፣ የቅርብ ጎረቤቶቻችን ከአገራችን ጋር የቋንቋ፣ የባህል፣ የታሪክ፣ የተፈጥሮ ሃብት ወዘተ ግንኙነት ያላቸው ናቸው፡፡ በአገራችን የሚካሄደው ለውጥ እነሱን በቀጥታ የሚነካ ሲሆን፣ በእነሱ ውስጥ የሚካሄደው ለውጥም የዚያኑ ያህል እኛን በቀጥታ የሚነካ ነው። ይህንኑ ዕውነታ ታሳቢ በማድረግ አገራችን ኢትዮጵያ ከአካባቢ አገራት ጋር በመልካም ጉርብትና፣ በትብብርና በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ ግንኙነት ስታራምድ ቆይታለች፤ አሁንም እያራመደች ትገኛለች፡፡ በዚህም ከኤርትራ በስተቀር ከሌሎች አጎራባች አገራት ጋር የጠበቀ ግንኙነት እና ትስስር መፍጠር ችላለች። ከኤርትራም ጋር ቢሆን የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን ማካሄድ ጀምራለች። አገራችን ኢትዮጵያ የአካባቢዋን ሰላም አስተማማኝ ለማድረግ ስትል ረጅም ርቀት ተጉዛለች፤ ሌሎች አገሮችን በማስተባበርም የላቀ ሚና ተጫውታለች። ለህዝቦች የጋራ ተጠቃሚነት የሚበጁ ትላልቅ ፕሮጀክቶችን እና የልማት እቅዶችን አውጥታ በመንቀሳቀስ፣ ጎረቤቶቿ በተቸገሩ ሰዓት በማስጠለል እና ያላትን ቆርሳ በማካፈል ለመልካም ጉርብትና እና የጥቅም ትስስር ጉልህ ሚና እየተጫወተች ያለች አገር ናት። በውጭ ጉዳይና አገራዊ ደህንነት ፖሊሲያችን ላይ እንደተመለከተው የቅርብ ጎረቤቶቻችንም ይሁኑ ሌሎች አገራትን አስመልክቶ የምንከተላቸው የፖሊሲና የስትራቴጂ ጉዳዮች የሚያጠነጥኑት ሰላማችንን፣ ፈጣን የኢኮኖሚ ልማታችንን እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታችንን በማረጋገጥ እና በማገዝ ላይ ነው፡፡ ይህም ሕዝቦቻችን በየደረጃው ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ፈጣን ልማትና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታን ዕውን ከማድረግ አኳያ የተመቻቸ ሁኔታ መፍጠር እና በአገራችን ህልውና ላይ ተጽዕኖ የሚያሳድሩ ሁኔታዎችን ማስወገድን ታሳቢ ያደርጋል፡፡  ከቅርብ ጎረቤቶቻችን ጋር የምንፈጥረው መልካም ግንኙነት እና ትብብር በውስጥ ጥንካሬያችን ላይ ተመስርቶ፣ ተመልሶ ለእኛው ትልቅ አቅም የሚፈጥርልን መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ሰሞኑን እንደተስተዋለው፣ በአገራችን የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ፍሰቱ ቀጥሏል፡፡ በግዙፍነታቸው የሚታወቁ የውጭ ኩባንያዎች ወደ አገራችን እየገቡ ይገኛሉ፡፡ ትላልቅ የንግድ ኤግዚቢሽኖች በውጭ እና በአገር ውስጥ መካሄዳቸው የቀጠለ ሲሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ አበዳሪ ተቋም እንዳረጋገጠውም ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ ዕድገቷ በአፍሪካ የመሪነቷን ቦታ ከጋና ትረክባለች፡፡ በቅርቡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ የአሜሪካ፣ የጀርመንና የእስራኤል ከፍተኛ ባለሥልጣናት በአገራችን ተገኝተው ያካሄዷቸው የሥራ ጉብኝቶች የሚያረጋግጡልንም፣ በአስቸጋሪ ወቅት ላይ በነበርንበት ጊዜ እንኳ አገራችን በሰላም፣ በዲፕሎማሲ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በሌሎችም ዘርፎች ተፈላጊነቷ እየጨመረ በመሄድ ላይ መሆኑን ነው፡፡ ለተፈላጊነታችን መጨመርም ዋነኛው ምክንያት በውስጣችን የፈጠርነው ጠንካራ አቅም መሆኑን መገንዘብ ያሻል፡፡ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በመደማመጥ እየፈታን እስከሄድን ድረስ በመላው ዓለም የሚኖረን ተሰሚነትና ተቀባይነት እየጨመረ መሄዱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ በመሆኑም፣ ውስጣዊ ችግሮቻችንን በሰላማዊ መንገድ እየፈታን፣ ዴሞክራሲያዊ አንድነታችንን እያጠናከርን፣ ልማታችንን ለማስቀጠል በአገራችን የተጀመረውን የለውጥ ሥራ ከዳር ለማድረስ እና የአገራችንን በጎ ገጽታ ለመገንባት መላው ሕዝባችን ከመንግስት ጎን ተሰልፎ እንዲረባረብ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም