ለፓርላማ ሴት አባላት የአመራር ክህሎት ስልጠና እየተሰጠ ነው

85

አዲስ አበባ  ጥር 25/2011 በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተመራጭ ሴቶች ኮከስ አባላትን የአመራር ክህሎት የሚያሳድግ ስልጠና በአዲስ አበባ እየተሰጠ ነው።

ስልጠናው በስልታዊ አመራርና በህግ የበላይነት ዙሪያ የሚያተኩር ሲሆን በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ አስተባባሪነት የተዘጋጀ ነው።

ኢትዮጵያ እያካሄደች ያለችውን ዘርፈ ብዙ የለውጥ ተግባራት በተለይም የሴቶችን ወደ አመራርነት የመምጣት ቀጣይነት ለማረጋገጥና ለማጠናከር ለምክር ቤት የተመራጭ ሴት የኮከስ አባላትን የአመራር ክህሎት ማሳደግ የስልጠናው ዓላማ ነው ተብሏል።

የጅስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ዳንኤል ገዛህኝ በዚህ ወቅት እንደገለፁት፤ ድርጅቱ የፍትህ አካላትን አቅም ለመገንባት በርካታ ተግባራትን ሲያከናውን መቆየቱን አውስተዋል።

ድርጅቱ ካከናወናቸው ተግባራትም፤ ደረጃውን የጠበቀ የማረሚያ ቤቶች ግንባታን ጨምሮ ለፖሊስ፣ ዐቃቢያን ህግ፣ ፍርድ ቤቶች፣ ለፓርላማ እና ለመስተዳድር አመራር አባላት የተለያዩ የክህሎት ማሳደጊያ ስልጠናዎችን ሲሰጥ መቆየቱን ለአብነት ጠቅሰዋል።

የህዝብ ተወካዮች ተግባር መንግስትን መቆጣጠር እና እርምጃ መውሰድ በመሆኑ ይህንን በጥራት ለመተግበር ከሚረዱ እገዛዎች መካከል በአመራርና በህግ የበላይነት ላይ ያተኮሩ ሥልጠናዎች አስፈላጊ ናቸው ብለዋል።

በመሆኑም ሴት የፓርላማ አባላት ያለባቸውን ኃላፊነት በመወጣት ረገድ የሚያጋጥሙ ውስጣዊና ውጪያዊ ችግሮች ለመፍታት ይህን የመሰሉ ስልጠናዎች ሚና ከፍተኛ አስተዋፆ አለው ነው ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ።

በምክር ቤቱ የተፈጥሮ ኃብት፣ ኢነርጂ እና መስኖ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ወይዘሮ ፈትያ ዩሱፍ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ሴት የፓርላማ አባላት በኃላፊነት ስሜት ስራዎችን እንዲሰሩ፣ ብቃታቸውን እንዲያጎለብቱና ተነሳሽነታቸውን እንዲያሳድጉ ጠቀሜታ እንደሚኖረው ገልፀዋል።

በተለይም በምክር ቤቱ ካሉት 10 ቋሚ ኮሚቴ ስብሳቢ አመራር አካላት ውስጥ አምስቱ ሴቶች በመሆናቸው ሴቶች በአመራር ዘርፍ ያላቸውን አቅምና ብቃት እንዲያሳድጉ ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ጠቁመዋል።

በተለይም የምክር ቤቱ ቋሚ ኮሚቴዎች ለሚያደርጉት የክትትልና የቁጥጥር ሥራ በስልታዊ አመራር  በጥበብና ማስተዋል ታግዞ ውሳኔዎችን እና እርምጃዎችን ለመውሰድ የሚያግዝ ሥልጠና መሆኑንም ጭምር አስረድተዋል።

በምክር ቤቱ የሴቶች ኮከስ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ወይዘሮ ብርቱካን ሰብስቤ ደግሞ፤ ስልጠናው መንግስት በእቅድ የያዛቸው ሥራዎች መሬት ላይ እንዴት እየተተገበረ መሆኑንና የግልጽነትና የተጠያቂነት አሰራር በአመራር ብቃት ውሳኔ ለመስጠት እድል እንደሚፈጥር ያላቸውን እምነት ገልፀዋል።

ለሁለት ቀናት በሚቆየው በዚሁ ስልጠና ከ70 በላይ የሚሆኑ የፓርላማ ሴት አባላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ጀስቲስ ፎር ኦል ፕሪዝን ፌሎውሺፕ ኢትዮጵያ መንግስታዊ ያልሆነ ግብረሰናይ ድርጅት ሲሆን በፍትህ ዘርፍ የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት የሚሰራ ድርጅት ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም