በደቡብ ክልል የተሰበሰበው ገቢ ከዕቅድ በታች ነው

103

ሀዋሳ ጥር 25/2011 በደቡብ ክልል ባለፉት ስድስት ወራት የተሰበሰበው ገቢ ከዕቅድ በታች መሆኑን የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን አስታወቀ።

''ግዴታዬን እወጣለሁ መብቴን እጠይቃለሁ'' በሚል መሪ ቃል ክልል አቀፍ የታክስ ንቅናቄ መጪው ሳምንት ጀምሮ ይካሄዳል ።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣንና የፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ በገቢ አሰባሰብ ሂደቱ ላይ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ አስረስ እንዳሉት በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ነበር ።

"መሰብሰብ የተቻለው 3 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ብቻ ነው" ብለዋል።

ለገቢ አሰባሰብ ዝቅተኛነት በክልሉ የተለያዩ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው የጸጥታ ችግር አንዱ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው የግብር ከፋዩ ኃላፊነትን የመወጣት ፍላጎት ማነስም ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል።

ሸማቹ ለሚፈጽመው ግዥና ለሚያገኘው አገልግሎት ተገቢውን ደረሰኝ አለመቀበሉ እንዲሁም የታክስ ማጭበርበርና ስወራ ተጨማሪ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

''ችግሩን ለመከላከል የተለያዩ እርምጃዎች ተወስደዋል" ያሉት ኃላፊው ለተጠቃሚ ደረሰኝ ያልሰጡ 100 የንግድ ተቋማት በነብስ ወከፍ 50 ሺህ ብር መቀጣታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል ።

በበጀት አመቱ ለመሰብሰብ የታቀደውን 11 ቢሊዮን ብር ሙሉ ለሙሉ ለማሳካት ከፊታችን ማክሰኞ ጀምሮ የግብር ንቅናቄ መድረክ እንደሚካሄድ አመልክተዋል።

የክልሉ ፋይናንስና ኢኮኖሚ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታምራት ዲላ በበኩላቸው በክልሉ ካለው አቅም አንጻር እየተሰበሰበ ያለው የገቢ መጠን አነስተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት 8 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር መሰብሰቡን ያሰታወሱት ኃላፊው፣ በክልሉ እስከ 15 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ እንደሚቻል በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋል።

"የክልሉ የወጪ ፍላጎት በዚህ በጀት ዓመት ወደ 37 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር አድጓል" ያሉት ኃላፊው፣ እየተሰበሰበ ያለው ገቢ ወጪውን በሚፈለገው መጠን አለመሸፈኑን ተናግረዋል ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም