የ''አፍረን ቀሎ'' የሙዚቃ ቡድን ወደ ተፀነሰበት ድሬዳዋ ገባ

82

ድሬዳዋ ጥር 24/2011 ለመላው ጭቁን ሕዝብ በተለይም ለኦሮሞ ሕዝብ ነጻነትና እኩልነት የታገለው የ''አፍረን ቀሎ'' የሙዚቃ ቡድን ወደ ተፀነሰበት ድሬዳዋ ምሽት ገባ።

የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጨምሮ የአስተዳደሩ አመራሮችና አድናቂዎቻቸው ከከተማው 18 ኪሎ ሜትር ድረስ በመውጣት ደማቅ አቀባበል አድርገውለታል፡፡

በአቀባበሉ ሥነ-ሥርዓት ላይ ምክትል ከንቲባ አብደላ አህመድ ''የሙዚቃ ቡድኑ አባላት የኦሮሞ ህዝብ አሁን እያጣጣመ ለሚገኘው ነጻነትና እኩልነት 'የማለዳ ቄሮ' በመሆን መስዋዕት ሆነዋል'' ብለዋል፡፡

የባንዱ አባላት በሥራዎቻቸው ሕዝቦች ከጭቆና አገዛዝ እንዲላቀቁና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት በአገሪቱ እንዲሰፍን መንቀስቀሳቸውን ገልጸዋል፡፡

አባላቱ በቆይታቸው በከተማዋ ለዘመናት ያሳለፉትን ኅብረት፣ ፍቅርና መተሳሰብን ለአዲሱ ትውልድ በማስተላለፍ የከተማው ወጣቶች አንድነታቸውን ጠብቀው የተሻለች ድሬዳዋ እንዲገነቡ ያነቃቃሉ ብለዋል፡፡

አቶ ዩሱፍ አህመድ የተባሉ የከተማው ነዋሪ ''ከረጅም  ዓመታት በኋላ የቡድኑን አባላትን ድሬዳዋ ላይ ማየቴ አስደስቶኛል'' ብለዋል፡፡

በአገሪቱ አሁን የተገኘውን ነፃነት፣ እኩልነትና ጅምር የዴሞክራሲሥርዓት ማየታቸው እንዳስደስታቸው የተናገሩት ደግሞ አዛውንቱ አቶ መሐመድ አብዱላሂ ናቸው፡፡

የቡድኑ አባል ድምፃዊ ሸንተም ሹቢሳ ለተደረገላቸው አቀባበል አመስግነው፣በአገሪቱ የተጀመረውን ሁሉን አቀፍ ለውጥ ከዳር ለማድረስ ዕውቀታቸውን፣ ገንዘባቸውንና ጉልበታቸውን በማስተባበር ድጋፍ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡

ወጣቱ አገራዊ ለውጡ ለማሳካት ተደራጅቶ እንዲንቀሳቀስም  ጠይቀዋል፡፡

ታዋቂዎቹን የክብር ዶክተር ዓሊ ቢራ ጨምሮ ዓሊ ሸቦና ሌሎች ታዋቂ አባላትን በማቀፍ በ1954 የተቋቋመው የሙዚቃ ቡድን ጨለንቆ ከተማ ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡

ቡድኑ ነገ  የምስራቅ ኢትዮጵያ ሕዝብ የሚታደምበት የሙዚቃ ኮንሰርት በድሬዳዋ ስታዲዬም ያቀርባል፡፡

በተያያዘ ዜና ባንዱ የሚያቀርበው የሙዚቃ ኮንሰርት በሰላም እንዲጠናቀቅ ወጣቱ ድጋፍና ጥበቃ እንዲያደርግ የድሬዳዋ ጊዜያዊ የፀጥታ ኮሚቴ ሰብሳቢ ብርጋዲዬር ጄኔራል ተስፋዬ ወልደማርያም አሳስበዋል፡፡

ብርጋዲዬር ጄኔራል ተስፋዬ ከወጣቶች ጋር ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በተወያዩበት ወቅት እንዳሳሰቡት ዝግጅቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ የከተማው ወጣቶች ተደራጅተው በኃላፊነት መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ኮሚቴው ዝግጅቱን ባማረና በሰላማዊ ሁኔታ ለማጠናቀቅ  ዝግጅት ማድረጉን  አስታውቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም