ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከመረጠን ህዝብ ጋር እንወያያለን-የምክር ቤት አባላት

1108

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 ወደተመረጡባቸው አካባቢዎች በመሄድ ለዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከህዝቡ ጋር እንደሚወያዩ አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ገለጹ።

የምክር ቤቱ አባላት ወቅታዊ የኢትዮጵያን የሰላምና ጸጥታ እንዲሁም የኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ ጥያቄዎችን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት አስተያየታቸውን የሰጡ የምክር ቤቱ አባላት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ የሰጡት ምላሽ የአገሪቱን ወቅታዊ ነባራዊ ሁኔታ በትክክል የሚያስረዳ፤ ህዝቡንም የሚያረጋጋ ነው ብለዋል።

በተያዘው ወር መጨረሻም ወደተመረጡባቸው አካባቢዎች በመሄድ በዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከመረጣቸው ህዝብ ጋር ውይይት እንደሚያደርጉ ነው የተናገሩት።

አስተያየታቸውን ከሰጡት ውስጥ ወይዘሮ ትብለጥ ገብረዮሐንስ ”የምክር ቤት አባላትም ወደ ምርጫ ክልላችን የመሄጃ ጊዜ ስለሆነ አሁን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የተባሉትንም ታች ያለውንም ተጨባጭ ሁኔታ አብሮ በመያዝ እኛም  ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት በማድረግ ከህብረተሰቡ የሚጠበቁ ነገሮችን እናስተላልፋለን።”

”ሰላማችንንም ሆነ ኢኮኖሚያችንን የሚጎዱ ነገሮችን የሚፈጽሙ የትኛውም ዜጎች መምከርና መመለስ ሰላሙንም ከህዝቡ በስተጀርባ ሆነው የሚያደፈርሱትን ወደ ሰለም እንዲመጡ ማድረግ ይጠበቅብናል” ያሉት ደሞ ወይዘሮ ታደለች ከበደ ናቸው፡፡

”ምክር ቤት በራሱ በኩል የሚሰራውን ስራ ይሰራል።የክትትል የቁጥጥር ህዝቡን የመምከር ወደ መስመር የመመለስ ስራዎችን መስራት አለብን ያሉት ደሞ  አቶ ብርሃኑ አበበ ናቸው፡፡