የጅቡቲ መንግስት ለውጭ አገር ዜጎች በሚሰጠው የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ክፍያ ኢትዮጵያውያን በልዩ ሁኔታ ይስተናገዳሉ

83

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 የጅቡቲ መንግስት ለውጭ አገር ዜጎች በሚሰጠው የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ክፍያ ኢትዮጵያውያን በልዩ ሁኔታ እንዲስተናገዱ ስምምነት ላይ መደረሱን የኢፌዲሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ገለፀ።

የሚኒስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብያት ጌታቸው በሰጡት መግለጫ በጅቡቲ የተካሄደው 15ኛው የኢትዮ- ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም ተጠናቋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁና የጅቡቲ ፕሬዝዳንት ኢስማኤል ኦማር ጌሌ በጅቡቲ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በተመለከተ ውይይት አድርገዋል።

በውይይታቸውም የጅቡቲ መንግስት ያወጣው አስገዳጅ የክፍያ ህግ የኢትዮጵያውያንን የመክፈል አቅም ባገናዘበ መልኩ ማሻሻያ እንዲደረግበት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ቃል አቀባዩ ገልጸዋል።

የጅቡቲ መንግስት የውጭ አገር ዜጎች የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ለማግኘትና ፈቃድ ለማሳደስ እስከ 200 ሺህ የጅቡቲ ፍራንክ እንዲከፍሉ በሚያስገድደው ህግ ላይ የማሻሻያ ጥያቄ ቀርቧል።

ይሁን እንጂ በጅቡቲ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክፍያው ከፍተኛ ተፅዕኖ ያለው መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ለፕሬዝዳንት ኢስማኤል በማስረዳታቸው በልዩ ሁኔታ እንዲታይ ከስምምነት ደርሰዋል።

ኢትዮጵያውያን የመኖሪያና የስራ ፈቃድ ለማውጣት እንዲሁም ፈቃዱን ለማሳደስ በሚያደርጉት እንቅስቃሴ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚ በሚሆኑበት መልኩ እንደሚከናወንም አቶ ነብያት ገልጸዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ትስስር ለማሳደግ ከኢትዮ-ጅቡቲ ድንበር እስከ ጅቡቲ ወደብ ድረስ ያለው መንገድ በቀጣዮቹ ሁለት ወራት የጥገና ስራ ይጀመራል።

ኢትዮጵያና ጅቡቲ ተመሳሳይ ባህልና ቋንቋ ያላቸው አገሮች መሆናቸውን የገለጹት አቶ ነብያት፤ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን ግንኙነት ለማጠናከር በጋራ ለመስራት ተስማምተዋል።

15ኛው የኢትዮ- ጅቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ከጥር 21 እስከ 23 ቀን 2011 ዓ. ም በጅቡቲ መካሄዱ ይታወቃል።

በሌላ በኩል በተለያዩ አገሮች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደህንነታቸው ተጠብቆ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ከዓለም አቀፉ የስደተኞች ድርጅት ጋር መንግስት በትብብር እየሰራ መሆኑም ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል።

ባለፉት ስድስት ወራት ከ65 ሺህ በላይ ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች ወደ አገራቸው መመለሳቸውን የገለጹት ቃል አቀባዩ፤ በቀጣይም ዜጎች ከሚገኙባቸው አገሮችና ተቋማት ጋር በትብብር እንዲመለሱ ይደረጋል ብለዋል።

ከግብጽ መንግስት ጋር በመግባባት በአስዋን ለእስር ተዳርገው የነበሩ 47 ኢትዮጵያውያን ከእስር የተፈቱ በመሆኑ በቅርቡ ወደ አገራቸው የሚገቡ ይሆናል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም