የምጣኔ ኃብት ችግሩን ለመፍታት የግብርናውን ዘርፍ ማዘመን የግድ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገለፁ

102

አዲስ አበባ ጥር 24/2011  በኢትዮጵያ ከመዋቅር ጋር በተያያዘ የሚስተዋለውን የምጣኔ ኃብት ችግር መከላከል የሚቻለው የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን በተለይም ደግሞ የመስኖ ልማትን በማስፋፋት መሆኑን መንግስት እንደሚያምን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዓብይ ገለፁ። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህን የገለፁት ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምላሽ በሰጡበት ወቅት ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት መንግሰት በከፍተኛ ወጪ ወደአገር ውስጥ የሚያስገባቸውን ስንዴንና ዘይትን የመሳሰሉ ምርቶች በአገር ውስጥ በማምረት የንግድ ሚዛኑን ለመጠበቅና ምጣኔ ኃብቱን ከጉዳት ለመታደግ የሚቻለው ሰፋፊ የመስኖ ልማት ፕሮጀክቶችን ማስፋፋትን ጨምሮ ዘርፉን በማዘመን ነው። 

ስራ አጥነትን፣ የዋጋ ግሽበትንና የወጪ ንግድ ሚዛን መዛባትን ጨምሮ በአገሪቱ ምጣኔ ኃብት ላይ የሚታዩትን የተለያዩ ችግሮች ለመፍታት እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒሰትሩ አስታውቀዋል። 

ላለፉት 15 ዓመታት በአማካይ አስከ 14 በመቶ ሆኖ የቆየውን የዋጋ ግሽበት ለመቆጣጠር በተወሰዱት እርምጃዎች ለውጥ መምጣቱን ጠቅሰው በአሁኑ ወቅት የግሽበቱ መጠን 10 ነጥብ 3 በመቶ ወርዷል ብለዋል።

የመንግስት ፕሮጀክት በጀትንና ባንኮች የሚሰጡትን ብድር በመቀነስ እንደዚሁም በሥራ ላይ ያሉ የተለያዩ የልማት ውጥኖች ኢኮኖሚውን ለተጨማሪ ወጪ እንዳይዳርጉ ለማድረግ በፍጥነት የሚጠናቀቁበትን መንገድ በማመቻቸት ግሽበቱ እንዲሻሻል ማድረግ ተችሏል ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ። 

መንግስት የኮንትሮባንድ ንግድን መከላከል የሚያስችሉ በርካታ ተግባራትን እንደሚያከናውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለዋል።

ባለፉት ጥቂት ጊዜያት የኮንትሮባንድ ንግድ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚና ሰላም በመናጋት ረገድ ትልቁን ድርሻ ይይዛል ሲሉም ተናግረዋል።

ከአገር ውስጥ የውጭ ምንዛሬ አቅም ሌሆኑ የሚችሉ ምርቶች በህገወጥ መንገድ ይወጣሉ፤ በምርቶቹ ሽያጭ ደግሞ ህገ ወጥ መሳሪያ ወደ ሀገር ቤት ይገባል ነው ያሉት።

መንግስት ይህን ተገንዝቦ ገቢዎችና ጉምሩክ አሰራሩ እንዲጠናከር እየሰራ መሆኑን ገልጸው፤ ተቋሙ በሚኒስቴር ደረጃ እንዲደረጃና በጥቂት ወራት ውስጥ ከ7 ሺህ በላይ ሰራተኞቹን በአዲስ ሪፎርም እነዲያዋቅር መደረጉን ለአብነት አንስተዋል።

በተጨማሪ የኮንትሮባንዲስቶችን የፋይናንስ ምንጭ ማድረቅ፤ ድንበር ላይ ያሉትን የጉምሩክ አሰራሮችን ማጠናከር፤ ከጎረቤት አገራት ጋር የጠረፍ ንግድ ስምምነት መፈራርም እንዲሁም ያለውን ግንኙነት በዲፕሎማሲ ማጠናከር ደግሞ በቀጣይ በትኩረት የሚሰሩ ተግባራት መሆናቸውን ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም