ዩኒቨርሲቲዎች የፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነቱን መወጣት አለበት- ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበይ አህመድ

1319

አዲስ አበባ ጥር 24/2011 የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የፖለቲካ ነጋዴዎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ ሁሉም ህብረተሰብ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አበይ አህመድ ጥሪ አቀረቡ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጥሪውን ያቀረቡት ዛሬ ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች በሰጡት ማብራሪያ ላይ ነው።

መንግስት የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ለፖለቲካ ጥቅም የማዋል ዝንባሌ እንደሚኖር ቀድሞ ተረድቶ  ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ውይይት ቢያደርግም  በተወሰኑ ተቋማት ግጭቶች ተከስተው የተማሪዎች ህይወት መጥፋቱን ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታሰዋል።

“በመሆኑም ተማሪዎች የማንም ፖለቲካ ኃይል ዓላማ ማስፈጸሚያ እንዳይሆኑ እራሳቸውን መጠበቅ አለባቸው” ሲሉ  ምክር ሰጥተዋል።

“ተማሪዎችን እሳት እያስጨበጡ የፖለቲካ የበላይነት ለማምጣት የሚፈልጉ ሃይሎች፤ ተግባራቸው ህገ-ወጥና ጊዜው ያለፈበት መሆኑን በመገንዘብ እጃቸውን ይሰብስቡ” ሲሉም አሳስበዋል።

ከተማሪዎች በተጨማሪ ሁሉም ህብረተሰብ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ከመሰል ሁኔታዎች ጸድተው የስልጠናና ምርምር ማዕከል እንዲሆኑ ኃላፊነታቸውን እንዲወጡም ጥሪ አቀርበዋል።

መንግስት አጥፊዎችን ለህግ ከማቅረብ በተጨማሪ የህግ የበላይነን ለማስፈን ከመቸውም ጊዜ በላይ  እየሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።