በአዲስ አበባ አግባብነት የሌለው ጭማሪ ባደረጉ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ ይወሰዳል ተባለ

72

አዲስ አበባ  ጥር 23/2011 በአዲስ አበባ  ከተማ በዳቦ ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ አግባብነት የሌለውና ህብረተሰቡን ያላማከለ ነው ሲሉ ነዋሪዎች ቅሬታቸውን አሰሙ ፡፡

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በበኩሉ  በዳቦ ዋጋ ላይ አግባብነት የሌለው ጭማሪ ባደረጉ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ  ገልጿል ።

ቢሮው በከተማዋ ባሉ ዳቦ ቤቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ምንም አይነት እውቅና ያልተሰጠውና አግባብነት የጎደለው በመሆኑ ይሄንን አድርገው በሚገኙ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ ገልጿል።

የዋጋ ጭማሪውን አስመልክቶ ኢዜአ በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች ላይ ባደረገው ምልከታ በትክክል የዋጋ ጭማሪ መኖሩን አረጋግጧል።

በዚህም ባለ 100 ግራም ዳቦ በ2 ብር ከ50 ሳንቲም፣ ባለ 200 ግራም ዳቦ በ5 ብር እንዲሁም ባለ 300 ግራም ዳቦ በ7 ብር ከ50 ሳንቲም እየተሸጠ እንደሚገኝ ተመልክቷል። 

አስተያየታቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት የሰጡ የመዲናዋ ነዋሪዎችም የተደረገው የዋጋ ጭማሪ አግባብነት የሌለውና ህብረተሰቡን ያላማከለ ነው ሲሉም ቅሬታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ።

በመሆኑም መንግስት ይህንን ተግባር በሚፈጽሙ አካላት ላይ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ እንደሚገባውም አስተያየታቸውን ገለጸዋል።

አቶ አክሊሉ ቢንያ አንድ ብር ከሰላሳ ሳንቲም ይሸጥ የነበረው ዳቦ ዛሬ ሁለት ከአምሳ ገብቷል፡፡ ይህ ደግሞ አግባብ አለመሆኑን ነው የተናገሩት

አቶ ጉታ አዱኛ በበኩላቸውየዳቦ ጭማሬው በጣም አስገራሚ እንደሆነ የከተማ አስተዳደሩ አስቸኮይ መፍቴህ ሊሰጠው እንደሚገባ ነው የተናገሩት

"የዳቦ ጭማሪው አግባብነት የለውም፤ በአንድ ጊዜ የ1 ብር ከ20 ሳንቲም ጭማሪ እግባብ አይደለም፤ ሁለተኛ ነገር መንግስት ባለበት አገር እንደዚህ አይነት ነገር ሲፈጸም መንግስት ምን እየሰራ ነው? ምንድነው እያደረገ ያለው አፋጣኝ የሆነ እርምጃ ሊሰጠው ይገባል።" ያለው ወጣት ዘላለም ጤናው ነው

የአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ መስፍን አሰፋ በበኩላቸው መንግስት ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በየወሩ 165 ሺህ ኩንታል በድጎማ ያቀርባል።

በዚህም በከተማዋ 1 ሺ 400 ከሚሆኑ ዳቦ ቤቶች ጋር ከ100 ግራም ጀምሮ በ1 ብር ከ30 ሳንቲም እንዲሸጡ የሚያደርግ ትስስር በመፍጠር እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል።

ይሁንና በአሁኑ ወቅት በከተማዋ ዳቦ ቤቶች ላይ የተደረገው የዋጋ ጭማሪ ምንም አይነት እውቅና ያልተሰጠውና አግባብነት የጎደለው መሆኑንም ተናግረዋል።

በዚህም በተተመነላቸው ዋጋ መሰረት የማይሸጡና ከዚህ ዋጋ በላይ ጨምረው በሚሸጡ ዳቦ ቤቶች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድም ጠቁመዋል።

በዚህም ቢሮው ባደረገው ክትልል በሁለት ቀናት ውስጥ በኮልፌ ክፍለ ከተማ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ አድርገው የተገኙ ሶስት ዳቦ ቤቶች እንዲሁም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አንድ ዳቦ ቤት ላይ እርምጃ መውሰዱን ጠቁመዋል።

ሌሎችም ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡና ህብረተሰቡን በአግባቡ እንዲያገለግሉና የተጣለባቸውን ሃላፊነት መወጣት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።

ህብረተሰቡም በሸቀጦች ላይ አላስፈላጊ ጭማሪን በሚመለከትበት ጊዜ ለሚያጋጥሙት ህገ-ወጥ ተግባራት በነጻ የስልክ መስመር 8885 ላይ ጥቆማ እንዲያደርግም ጥሪያቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም