በትብብርና መቻቻል ላይ የተመሰረተ ዓለም መፍጠር ይገባል - የተባበሩት መንግስታት ድርጅት

82

አዲስ አበባ ጥር 23/2011 መንግስታት ከጥላቻና ቂም በቀል ፖለቲካ ወጥተው የዜጎችን መፃኢ እጣ ፋንታ በትብብርና መቻቻል ላይ የተመሰረተ ለማድረግ መስራት እንዳለባቸው አንድ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊ ገለፁ።

የጀርመኑ አምባገነናዊ መሪ አዶልፍ ሂትለር በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት ከስድስት ሚሊዬን የሚልቁ አይሁዶችና ሌሎች አያሌ ንጹሃን ዜጎች በግፍ አልቀዋል። 

የናዚ ቡድን ከ74 ዓመት በፊት ያደረሰውን ይህንን እልቂት የሚዘክር መርሃ ግብር ዛሬ በአዲስ አበባ የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን ተከናውኗል።

በመርሃ ግብሩ በወቅቱ የነበሩ የተጎጂ ቤተሰቦች፣ በኢትዮጵያ የእስራኤልና ጀርመን አምባሳደሮች እንዲሁም ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራምና ሰብዓዊ እርዳታ በኢትዮጵያ አስተባባሪ አኒያስ ቹማ በስነ-ስርዓቱ ላይ ንግግር አድርገዋል።

እርሳቸው እንዳሉት፤ ናዚዎች በአይሁዳዊያንና ሌሎች ንጹሃን የሰው ፍጡሮች ላይ የፈፀሙትን ዓይነት ግፍ በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች በተለያዩ የዓለም ክፍሎች መፈፀማቸውን ታሪክ መዝግቧል።

በሰው ልጆች ላይ የሚደርሰው ስቃይና እንግልት መቋጫ እንዲያገኝ መንግስታት ንጹሃን ዜጎችን የፖለቲካ መጠቀሚያ ከማድረግ ተቆጥበው ስለ አንድነትና ትብብር መስበክ አለባቸው ሲሉም አሳስበዋል።

የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በመጠቀም ቂም በቀልና ጥላቻ ከመዝራት ልዩነቶችን በማክበር በአንድነት መስራት በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል ብለዋል።

በኢትዮጵያ፣ ቡሩንዲና በርዋንዳ የእስራኤል አምባሳደር ራፋየል ሞራቭ ያለፈው ኢ-ሰብዓዊ ድርጊት የሚታወሰው ለበቀልና ጥላቻ ሳይሆን ወደፊት እንዳይደገም ለመማሪያ መሆኑን ገልጸዋል።

"እኛ ለዜጎች ክብርና እኩልነት በትብብር ስንሰራ ደህንነቷ የተረጋገጠ፣ ተቀባይነት ያላትና ነጻ አለም እየገነባን ለትውልድ እያስተላለፍን መሆኑን መገንዘብ ይኖርብናል" ብለዋል።

የአውሮፓ ህብረት "በልዩነት አንድ መሆን አለብን"  የሚለው መሪ ሃሳብ በአግባቡ በመተግበር በአለም ህዝቦች ሰላም፣ ፍቅርና አንደነት ማስፈን ይገባል ሲሊም ገልፀዋል።

ኢትዮጵያ ልዩነቶችን እንደ ጌጥ በመጠቀም ዜጎች በመቻቻል ላይ የተመሰረተ አንድነት እንዲኖራቸው በማድረግ በምሳሌነት የምትጠቀስ መሆኗን የገለጹት አምባሳደሩ፤ ሌሎች ዓለማትም ከዚህ መማር እንዳለባቸው ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የጀርመን አምባሳደር ብሪታ ዋግነር በበኩላቸው የጀርመን መንግስት በናዚ አስተዳደር በዜጎች ላይ የደረሰው እልቂት እንዳይደገም በፓርላማ ደረጃ "አይደገምም" በሚል መርህ እንዲዘከር ያደርጋል ነው ያሉት። 

በአለም ላይ ፍቅር፣ ሰላም፣ አንድነትና የጋራ እድገት እንዲኖር መንግስታት የጥላቻና ዘረኝነት አስተሳሰብን በማውገዝ ስለ አንድነትና ትብብር እንዲያስትምሩ ጠይቀዋል። "እንዲህ ዓይነቱ ሁኔታ ሲከሰትም ደምፃችንን በማሰማት ችግሩን ከጥንስሱ ለመቅጨት መታገል ይገባል" ብለዋል።

ጥቂት ቡድኖች ወይም ግለሰቦች ፍላጎታቸውንና ጥቅማቸውን ለማስከበር በሚያደርጉት እኩይ ተግባር ንጹሃን ዜጎች እንዳይጎዱ የትውልድ አደራችንን እንወጣ  ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም