ለተፈጥሮ ሀብት ክብካቤ የአርሶ አደሩ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ ወሳኝ ነው---የኦሮሚያ ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ

86

መቱ ጥር 23/2011 በኢሉአባቦር ዞን የሚገኘውን የተፈጥሮ ሀብት ጠብቆ ለማቆየት አርሶ አደሩ የጀመረውን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የኦሮሚያ ክልል ግብርና እና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ አስታወቀ።

የክልሉ መንግስት የስራ ሀላፊዎች በኢሉአባቦር ዞን የተለያዩ ወረዳዎች እየተከናወነ ያለውን የበጋ ወቅት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

በጉብኝቱ ላይ የቢሮ ኃላፊው አቶ ዳባ ደበሌ እንዳሉት የአካባቢውን የተፈጥሮ ሀብት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ለማስተላለፍ  አርሶ አደሩ የጀመረውን የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ  አጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል።

“የልማት ስራው የዞኑን የደን ሽፋን ወደ ነበረበት ለመመለስ ለሚደረገው ጥረት ትልቅ ሚና አለው” ያሉት የቢሮ ሀላፊው አርሶ አደሩ  የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የዞኑ አርሶአደሮች የተፈጥሮ በመንከባከብ ለደን ሽፋኑ መጨመር እያደረጉት ባለው ጥረት የክልሉ መንግስት ምስጋና እንደሚያቀርብም ገልጸዋል፡፡

የኢሉአባቦር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ነመራ ቡሊ በበኩላቸው በዞኑ 13 ወረዳዎች ካለፈው ሳምንት ጀምሮ  262 ተፋሰሶችን ተከትሎ በሚገኝ 128ሺህ ሄክታር መሬት ላይ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ እየተካሄደ ነው።

191ሺህ የሚሆኑ አርሶ አደሮችን በማሳተፍ እየተካሄደ ባለው የልማት ስራ ከ27ሺህ ኪሎ ሜትር በላይ የእርከንና ጎርፍ መቀልበሻ ቦይ ለማከናወን መታቀዱን ገልጸዋል።

በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያት የተጎዳ ከ15ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ከሰውና እንስሳት ንክኪ ተከልሎ እንደሚጠበቅም ነው የተናገሩት፡፡

አርሶ አደሩ ለመጪው የግብርና ወቅት ልማት ማሳውን በወቅቱ እንዲያዘጋጅ የጀመረውን የተፋሰስ ልማት ስራ በተቀመጠው የግዜ ገደብ በፍጥነት ማጠናቀቅ እንዳለበትም አስገንዝበዋል፡፡

የያዮ ወረዳ አርሶ አደር ደሴ በርኬሳ እንዳሉት የአፈርና ወሀ ጥበቃ ስራ ከጀመሩ ካለፉት ስድስት አመታት ወዲህ በማሳቸው ላይ የአፈር መሸርሸር በመቀነሱ የሰብል መቀጨጭ ችግር እየተቃለላቸው ይገኛል።

“በአሁኑ ወቅት ከጠቀሜታው የተነሳ ለልማቱ ፍላጎትና ተነሳሽነት ቢጨምርም የተፋሰስ ልማት ባህል ሆኖ እንዲቀጥል ለወጣቱ ተከታታይ ግንዛቤ ሊሰጥ ይገባል” ብለዋል፡፡

በበጋው ወቅት በሚያከናወኑት የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ ክረምት ላይ የደንና የሳር ዝርያዎችን መትከላቸው የአካባቢ ልምላሜ እንዲጨምርና በቅርበት የእንስሳት መኖ እንዲያገኙ እንዳደረጋቸው የተናገሩት ደግሞ ሌላኛው የቀበሌው አርሶ አደር  ተስፋዬ ፍሪሳ ናቸው፡፡

“የደን መጠኑ እንዲጨምር ችግኝ ከመትከል ባለፈ በጋራ በመሆን ጥበቃና እንክብካቤ እያደረግን ነው” ብለዋል።

በኢሉ አባቦር ዞን ባለፉት ስድስት አመታት 326ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት ላይ አርሶ አደሩን ያሳተፈ የአፈርና ውሀ ጥበቃ ስራ መከናወኑን ከዞኑ ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የተገኘ መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም