የኢትዮ-ጂቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ተጠናቀቀ

851

አዲስ አበባ ጥር 23/2011 ከጥር 21 ቀን 2011 ዓ.ም ጀምሮ በጂቡቲ ሲካሄድ የቆየው የኢትዮ-ጂቡቲ የሚኒስትሮች የጋራ ኮሚሽን ስብሰባ ዛሬ ተጠናቋል።

ስብሰባው በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ እና በጂቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሞሀመድ አሊ የሱፍ መሪነት ሲካሄድ መቆየቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

ዶክተር ወርቅነህ ባደረጉት የስብሰባ መዝጊያ ንግግር ለሶስት ቀናት ሲካሄድ የነበረው ምክክር በመግባባትና በወዳጅነት ላይ የተመሰረተና በቀጣይ ለሚሰሩ ስራዎች ወሳኝ አቅጣጫ ያስቀመጠ መሆኑን ገልጸዋል።

በመግባቢያ ቃለ ጉባኤው መሰረት የውጭ ጉዳይና የሚመለከታቸው አካላት የቅርብ ክትትል በማድረግ መግባባት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ አሳስበዋል።

በሁለቱ አገሮች መካከል የተፈጠረው የኢኮኖሚ ትብብር ለቀጠናው ውህደት ጠንካራ መሰረት የጣለ መሆኑንም ሚኒስትሩ በንግግራቸው አስገንዝበዋል።

በመግባቢያ ሰነዱ ስምምነት የተደረሰባቸው ጉዳዮች ወደ ተግባር በሚቀየሩበት ወቅት የሚያጋጥሙ እንቅፋቶችን የግድ የጋራ ኮሚሽን ስብሰባን ሳይጠብቁ በየጊዜው በባለሙያዎች እየፈተሹ ተግባር ላይ ማዋል እንደሚገባ አመልክተዋል።

የጂቡቲ የውጭ ጉዳይና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር ሙሀመድ አሊ የሱፍ በበኩላቸው በሁለቱ አገሮች መካከል በቀጣይ በጋራና በትብብር መሰራት ያለባቸው ጉዳዮችን በዝርዝር በመለየት ወደ ስራ ለመቀየር የሚያስችል የመግባቢያ ቃለ ጉባኤ በስብሰባው ማጠቃለያ ላይ መፈረሙ የጎላ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።

በመግባቢያ ቃለ ጉባኤው የተቀመጡ ነጥቦችን ወደ ተግባር በመለወጥ የሁለቱን አገሮች ህዝቦች የሚጠቅሙ ተጨባጭ ስራዎችን ማከናወን ወሳኝ መሆኑንም አስገንዝበዋል።

በጋራ ኮሚሽን ስብሰባው የሁለቱ አገሮች ውጭ ጉዳይ፣ የገቢዎች፣ የንግድ እንዲሁም የትራንስፖርት ሚኒስትሮችና ሚኒስትር ዴኤታዎች ተገኝተዋል።