ኢትዮጵያና ኖርዌይ በተለያዩ መስኮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ

66
አዲስ አበባ  ሚያዚያ 26/2010 ኢትዮጵያና ኖርዌይ በጤና፣ በትምህርትና በሰብዓዊ እርዳታ መስኮች በጋራ ለመስራት ተስማሙ። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር አክሊሉ ኃይለሚካኤል የኖርዌይ አቻቸውን ጀንስ ፍሮሊች ሆልቴን ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው አነጋግረዋል። ዶክተር አክሊሉ እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያና ኖርዌይ እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር ከ1947 ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት አላቸው። የሁለቱ አገራት ግንኙነት ከቅርብ ጊዜ ወዲህም ይበልጥ እያደገ መምጣቱን ገልጸው በተለይም በትምህርት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በመልካም አስተዳደር ግንባታ ከኖርዌይ ጋር ጠንካራ ትስስር መኖሩን ተናግረዋል። በቅርቡ ያራ ኢንተርናሽናል ፋውንዴሽን የተሰኘ የአገሪቱ ኩባንያ በኢትዮጵያ ማዳበሪያ ለማምረት የሚያስችል የአንድ ቢሊዮን የአሜሪካ ዶላር ስምምነት ተፈራርሟል። ይህም በከፍተኛ ደረጃ ማዳበሪያ ለመግዛት የሚውለውን የውጭ ምንዛሪ እንደሚያድነው ነው ሚኒስትር ዴኤታው የተናገሩት። የኖርዌይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ሚስተር ጀንስ ፍሮሊች ሆልቴም፤ ኢትዮጵያና ኖርዌይ ለረጅም ዘመናት የዘለቀ ወዳጅነት እንዳላቸው አንስተዋል። ኖርዌይ ከኢትዮጵያ ጋር በፖለቲካ፣ በልማት ሥራዎችና በሚሽነሪዎቿ ጠንካራ ትስስር ለመፍጠር እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በ1995 ስምምነት ተፈራርማ ነበር። ኢትዮጵያ ኖርዌይ ትኩረት ከምታደርግባቸው አገራት መካከል አንዷ ስትሆን አዲስ አበባ የሚገኘው የአገሪቱ ኤምባሲ በአፍሪካ ዋንኛው ማዕከል መሆኑን ከኤምባሲው የተገኘው መረጃ ያመለክታል። ኢትዮጵያና ኖርዌይ በሰላምና ፀጥታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በጾታ እኩልነት፣ በስደተኞች አስተዳደር፣ በትምህርትና በዘላቂ ልማት በትብብር የሚሰሩ ሲሆን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለፈው ዓመት ወደ ኦስሎ ከአፍሪካ የመጀመሪያውን የቀጥታ በረራ አድርጓል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም