103 የሪል ስቴት አልሚ ኩባንያዎች የቤት ግብር እየከፈሉ አይደለም

121

አዲስ አበባ ጥር 22/2011 መቶ ሶስት የሚጠጉ የሪል ስቴት አልሚ ኩባንያዎች የቤት ግብር እየከፈሉ አለመሆኑ ተገለፀ።

ይህ የተገለፀው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከሪል ስቴት አልሚ ኩባንያዎች ጋር ለሁለተኛ ጊዜ ተገናኝቶ በመከረበት ወቅት ነው።

የከተማ አስተዳደሩና የሪል ስቴት ኩባንያዎቹ ከዚህ ቀደም ባደረጉት ምክክር ከዘርፉ ጋር ተያይዞ የሚነሳውን የሊዝ ፣ የይዞታና መሬትን በህገ ወጥ መንገድ አጥረው ያስቀመጡትን ህጋዊነት እንዲፈትሽ ከሁሉም የባለድርሻ አካላት የተውጣጣ ግብረሃይል ተቋቁሞ ነበር።

ይሄው ግብረሃይል በቦሌ ፣ በየካ እና በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፍተሻ ሲያደርግ ቆይቶ በዛሬው ዕለት የደረሰበትን ለሪልስቴት አልሚ ባለቤቶችና ባለድርሻ አካላት አቅርቧል።

በመሆኑም ግብር ኃይሉ በ130 ሪል ስቴቶች ባደረገው የመረጃ ማጣራት ሥራ 6 ሪል ስቴቶች የቤት ግብር እየከፈሉ ያሉ መሆኑን እና 21 ሪል ስቴቶች ደግሞ መክፈል ጀምረው ያቋረጡ ሲሆን 103 ሪል ስቴቶች ግን ምንም አይነት ክፍያ ያልጀመሩ መሆናቸውን አረጋግጧል።

በዚህ መሰረት ከ4 ሚሊዮን 433 ሺህ 468 ካሬ ሜትር ቦታ ላይ መሰብሰብ የሚገባው የቤት ግብር ገቢ ያሳጣ መሆኑ ታውቋል።

በተጨማሪም ከተፈቀደላቸው ይዞታ በላይ አስፋፍተው የያዙ፣ የሊዝ ግብር ያልከፈሉ ፣ ግንባታ ጀምረው ያቆሙ፣ ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጪ መሬቱን የሚጠቀሙና መሬትን ለሶስተኛ ወገን ያስተላለፉ ኩባንያዎች መኖራቸውም ተገልጿል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የከተማው ምክትል ከንቲባ ኢንጅነር ታከለ ኡማ፤ የሪልስቴት ዘርፉ የመዲናዋን የቤት ችግር ለመፍታት አጋዥ መሆኑን ገልፀዋል።

ዘርፉ ህግን ተከትለው የሚሰሩ የሪልስቴት አልሚዎች እንዳሉት ሁሉ ህገ-ወጥ ተግባራትን እየከወኑ ያሉ ኩባንያዎች መኖራቸውንም ጠቁመው በህገ ወጦች ላይ ዕርምጃ እንደሚወስድም አስገንዝበዋል፡፡

የሪልስቴት አልሚ ኩባንያዎች የሚጠበቅባቸውን የሊዝ፣ የቤት ግብር እና ተያያዥ ክፍያዎች እንዲያጠናቅቁም ጭምር አስገንዝበዋል።

የሪልስቴት አልሚ ኩባንያዎች ጊዜ ሳይወስዱ በየክፍለ ከተማቸው በመገኘት የድርጅታቸውን ፋይል በህጋዊ መልኩ እንዲያደራጁ ያሳሰቡ ሲሆን ይህ ካልሆነ ግን በየቦታው ያሉ የሪልስቴት ቤቶች ባለቤት አልባ እንደሆኑ በመቁጠር የከተማ አስተዳደሩ እርምጃ እንደሚወስድባቸው አሳስበዋል።

የተቋቋመው ግብረ ኃይል በሁለት ሳምንታት ውስጥ የቀሩ ሪል ስቴቶችንና በራሳቸው መሬት ገዝተው የሚያለሙ አልሚዎች ያሉበትን ህጋዊ አካሄድ፣ የግንባታ ደረጃና ያለባቸውን ችግር እንዲፈትሽም ጠይቀዋል፡፡

የንብረት ገቢ ግብር /property tax/ገቢ በብዙ የዓለም ከተሞች የጀርባ እጥንት እንደሆነ የሚነገርለት የከተማ ነክ ታክስ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም