ኮሚሽኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የምርመራ ውጤቶች ሥራ ላይ እንዲውሉ መስራት ይኖርበታል-ምክር ቤቱ

77

አዲስ አበባ ጥር 22/2011 የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በአገሪቷ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መርምሮ የሚያገኘው ውጤት ሥራ ላይ እንዲውል መስራት እንደሚኖርበት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሳሰበ።       

የምክር ቤቱ የሕግ፣ ፍትህና ዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የኮሚሽኑን የ6 ወራት እቅድ አፈጻጸም ዛሬ ገምግሟል። 

ምክትል ዋና ኮሚሽነሩ አቶ እሸት ገብሬ ሪፖርቱን ሲያቀርቡ በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የኀብረተሰቡ ግንዛቤ አናሳ በመሆኑ ኮሚሽኑ ግንዛቤ ማስጨባጫ ሥራዎች ላይ ትኩረት አድርጎ እየሰራ ነው ብለዋል።   

ባለፉት ስድስት ወራትም 6 ሺህ 635 የሚሆኑት የፖሊስ አባላት፣ ተጠርጣሪዎች፣ የማረሚያ ቤት አስተዳደሮች አካላትና ታራሚዎች፣ የጤና ባለሙያዎች፣ ተማሪዎች፣ መምህራንና የኃይማኖት መሪዎች እንዲሁም የአገር ሽማግሌዎች ስልጠናውን ከወሰዱ መካከል ናቸው።

ከመብት ጥሰት ጋር በተያያዘም 1 ሺህ 229 አቤቱታዎች መቅረባቸውን የገለጹት ምክትል ኮሚሽነሩ፤ 753 በወንዶች፣ 287 ጉዳዮች በሴቶችና 256 ጉዳዮች ደግሞ በቡድን የቀረቡ መሆናቸውን ገልጸዋል።  

ከዚሁ ውስጥ 261 አቤቱታዎች በምርመራና በድርድር እንዲሁም በመጀመሪያ ደረጃ መፍትሄ ያገኙ ሲሆን በማስረጃ አለመኖርና በባለጉዳይ መጥፋት ምክንያት 13 አቤቱታዎች ተዘግተዋል።   

አቶ እሸት እንደሚሉት የሎጂስቲክ አገልግሎት እጥረት፣ የበጀትና በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰተው የጸጥታ ችግር ስራው በሚፈለገው መጠን እንዳይጓዝ አድርጓል። 

የምክር ቤቱ አባላት በበኩላቸው ተቋሙ የምርመራ ውጤቱ ሥራ ላይ እንዲውል መስራት አለበት፣ ስልጠና መስጠት ብቻውን ውጤታማ ማድረግ አይችልም፤ ውጤቶች ላይ ትኩረት መደረግ አለበት፣ ተቋሙ የሚያቀርባቸው ምክረ ሀሳቦችም እንዲፈጸሙ የሚጠበቅበትን ኃላፊነት ሊወጣ ይገባል የሚሉ ሀሳቦችን አንስተዋል።  

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ወይዘሮ ፎዝያ አሚን እንደተናገሩት፤ ኮሚሽኑ በአገሪቷ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰት የምርመራ ውጤቶች ለምክር ቤት ሕጋዊ አሰራሩን ጠብቆ መቅረብ ሲገባው አልቀረበም።      

ይህም ሰብአዊ መብት ላይ የሚፈለገው ውጤት እንዳይመጣ እያደረገ መሆኑን ገልጸው በቀጣይ ተቋሙ ከምክር ቤቱ ጋር ተናቦ መስራት አለበት ሲሉም አሳስበዋል።  

ኮሚሽኑ በርካታ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎችን ቢያከናውንም  የሚፈለገውን ያህል ውጤት አላመጣም የሚሉት ሰብሳቢዋ ወደ ተቋሙ ከመጡት 1 ሺህ 296 አቤቱታዎች ውስጥ 788ቱ በኮሚሽኑ ስልጣንና ተግባር ውስጥ የማይወድቁ ናቸው ተብለው መመለሳቸው እንደማስረጃ ያቀርባሉ።

''ስለጠናዎች ከተሰጡ በዚህ ደረጃ የሚመጣው አቤቱታዎች ቁጥር መቀነስ ነበረበት'' ያሉት ወይዘሮ ፎዚያ በቀጣይ የሚሰጡ ስልጠናዎች መርሃ ግብሮቹ ውጤት በሚያመጣ መልኩ መሆን አለባቸው ሲሉ ያስገነዝባሉ። 

ለ265 አቤቱታዎች ደግሞ የምክር አገልግሎት ሰጥቼ ሸኝቻለሁ በሚል ተቋሙ ያቀረበው ሪፖርትም ተገቢ እንዳልሆነ አመልክተው ''የሰብአዊ መብት ጥሰት በሚደረግበት አገር ላይ ምክር ሰጥተናል ብሎ ማቅረብ ተገቢ ነው ወይ?'' ሲሉም ጠይቀዋል።  

ኮሚሽኑ በተለይ ተጠያቂነት ማስፈን ላይ ክፍተት እንዳለበት የተናገሩት ሰብሳቢዋ በምርመራ ሂደት ተጠያቂ ሆነው የሚለዩ አካላት  እርምጃ እንዲወሰድባቸው ለሚመለከተው አካል ማቅረብ ላይ አበክሮ ሊሰራ ይገባል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም