ፓርኩን በዓለም ቅርስነት በቋሚነት ለማስመዝገብ ባለድርሻዎች አካላት ሚናቸውን እንዲወጡ ተጠየቀ

78

ጎባ ጥር 21/2011 የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክን በቋሚነት በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ  ባለድርሻ አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ዱር እንስሳት ልማትና ጥበቃ ባለሥልጣን ጠየቀ።

ባለድርሻ አካላት የተሳተፉበት የንቅናቄ መድረክ በባሌ ጎባ መካሄድ ጀምሯል።

የባለሥልጣኑ  ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን መኮንን በመድረኩ ላይ እንደገለጹት ፓርኩን በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/በቋሚነት ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት ለማፋጠን ባለድርሻዎች የሚጠበቅባቸውን ተግባር ሊፈጽሙ ይገባል።

ባለድርሻ አካላት የአካባቢው ነዋሪዎች በፓርኩ ውስጥ ኑሮአቸውን በመመስረታቸው በብርቅዬ አጥቢ እንስሳት፣አዕዋፍና እፅዋት ዝርያዎች ላይ እየደረሰ ያለውን ጉዳት ለማስቀረት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ባለድርሻ አካላት ፓርኩን በቋሚነት በድርጅቱ ለማስመዝገብ የሚደረገውን ጥረት እንዲያግዙ መድረኩ መዘጋጀቱን አመልክተዋል።

የባሌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ኢብራሂም ሐጂ በበኩላቸው ባለድርሻ አካላት በፓርኩ የሚገኙ የዱር እንስሳትን ጨምሮ ብዝሃ ሕይወትን ለመጠበቅና ለማልማት በሚደረገው ጥረት ሁሉም አካላት ድርሻቸውን እንዲወጡ አሳስበዋል።

ዞኑ ፓርኩን በዓለም ቅርስነት ለማስመዘገብ በሚደረገው ጥረት በየደረጃው የሚገኙ የአስተዳደር እርከኖችን በማስተባበር ኃላፊነቱን ይወጣል ብለዋል።

በመድረኩ የፌዴራልና የክልሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ጨምሮ ከመንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ተወካዮች በመሳተፍ ላይ ናቸው።

የባሌ ተራሮች ብሔራዊ ፓርክ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2009 በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት/ዩኔስኮ/ በጊዜያዊ መዝገብ ላይ  ሰፍሯል።

በኦሮሚያ ክልል ውስጥ የሚገኘው ይህው ፓርክ በ1962 የተመሰረተ ሲሆን ፣ ከአዲስ አበባ በ4ዐዐ ኪሎ ሜትር ርቀት ይገኛል፡፡

የፓርኩ  ጠቅላላ ስፋት ወደ 2ሺህ 2ዐዐ ኪሎ ሜትር ስፋት እንዳለው መረጃዎች ያመለክታሉ። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም