ከጭልጋና አካባቢው ለተፈናቀሉ ወገኖች 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ድጋፍ ተደረገ

55

ጎንደር ጥር 21/2011 በማዕከላዊ ጎንደር በጭልጋና አካባቢው በተፈጠረው ግጭት ለተፈናቀሉ ወገኖች ማቋቋሚያ 1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ብር የሚጠጋ የገንዘብና የቁሳቁስ ድጋፍ ተበረከተ፡፡

የዞኑ አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት የቅድሚያ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ አቶ አብደላ ኑር ሁሴን እንደተናገሩት ለተፈናቃዮቹ  ድጋፉን ያደረጉት በከተማው የሚገኙ ተቋማትና ግለሰቦች ናቸው።

በዚህም የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

በተጨማሪም ጅጋን ኮሌጅ ግምታቸው 150ሺህ ብር የሚያወጡ 500 የቤት ክዳን ቆርቆሮ ሰጥቷል፡፡

ወጣት ሐብታሙ ያለው የተባለ ግለሰብ በአይምባና በትክል ድንጋይ ጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች በ140ሺህ ብር ወጪ የገዛቸውን 400 ብርድ ልብሶች ማስረከቡን ገልጸዋል፡፡

ወጣቱ ቀደም ሲል ከቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ተፈናቅለው በነቀምቴ መጠለያ ለሚገኙ ተፈናቃዮች 40 ኩንታል ዱቄት መስጠቱንም አስታውሰዋል።

በዞኑ ከሁለት ወራት በፊት በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ 40ሺ ሰዎች በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች እንደሚገኙ ከዞኑ አደጋ መከላከል ጽህፈት ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም