“የተቆራረጠው የትምህርት መርሃ ግብር በውጤታችን ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል”- የወላይታ ዞን የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች

1123

ሶዶጥር20/2011በተለያዩ ምክንያቶች የተቆራረጠው የትምህርት መርሐ ግብር በውጤታቸው ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚል ስጋት እንዳላቸው የወላይታ ዞን የ10ኛና የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ተናገሩ።

የወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ የማካካሻ ሥርዓት በመዘርጋት የመማር ማስተማር ሥራውን እያከናወነ መሆኑን አስታውቋል።

የክፍሎቹ አንዳንድ ተማሪዎች ለኢዜአ እንደገለጹት በዚህ ዓመት የሚጠብቋቸው አገር አቀፍ ፈተናዎች ውጤታቸውን ላይ ተጽዕኖ የሳድራል የሚል ስጋት አድሮባቸዋል።

በየጉኑኖ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የ10ኛ ክፍል ተማሪው ተመስገን በቀለ ዘንድሮ በተለያዩ ምክንያቶች የተቆራረጠው ትምህርት በአገር አቀፍ ደረጃ በሚሰጡት ፈተናዎች ወጤት ላይ ተጽዕኖ ያሳድራል የሚል ስጋት እንዳለው ተናግሯል።

የበዴሳ ሁለተኛ ደረጃና መሰናዶ ትምህርት ቤት የተፈጥሮ ሳይንስ ተማሪው አብያለው ከፈለኝ በበኩሉ መምህራን ለመንግሥት ያቀረቧቸውን ጥያቄዎች ተከትሎ ትምህርት ተቋርጦ እንደነበር አስታውሶ፣ይህንን ተከትሎ ተከታታይ የክፍል ምልከታ፣ጥናትና የተግባር ልምምድ ጉድለቶችን ስለሚያስከትል ውጤቴ ላይ ስጋት አድሮብኛል ብሏል፡፡

በሶዶ መሰናዶ ትምህርት በማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የ12ኛ ክፍል ተማሪ ቃልኪዳን በለጠ ለሴቶችና በትምህርታቸው ዝቅተኛ ውጤት ለሚያመጡ ተማሪዎች ይሰጥ የነበረው ልዩ ድጋፍ አነስተኛ መሆኑን ተናግራለች።

በወላይታ ዞን ትምህርት መምሪያ የፈተና ዝግጅት አስተዳደር የትምህርት ምዘናና ጥናት ዳይሬክተር አቶ መርክነህ ዲሳ ከመምህራን፣ከተማሪዎችና ከወላጆች ጋር በተደረገው ውይይት የባከነውን የትምህርት ጊዜ ለማካካስ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የማበረታቻና የተጠያቂነት አሰራርን በመዘርጋት ከትምህርት ቤት ኃላፊዎችና መምህራን ጋር ስምምነት ተደርሶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቆመዋል።

ለመጀመሪያው መንፈቅ ዓመት መሸፈን የሚገባዉ የትምህርት ይዘት ተጣርቶ ዞናዊ ፈተና መዘጋጀቱን የገለጹት አቶ መርክነህ፣ ይህንን መነሻ በማድረግ ተማሪዎችን ለአገር አቀፍ ፈተና ብቁ ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በዞኑ በዚህ ዓመት  የሚሰጡትን አገር አቀፍ ፈተናዎች ለመውሰድ ከ99 ትምህርት ቤቶች የሚማሩ ከ35 ሺህ 200 ሺህ በላይ ተማሪዎች  በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።