የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ ከአገሪቷ አልፎ የአፍሪካን መልካም ስም የሚገነባ ነው - የጀርመን ፕሬዚዳንት

76

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 በኢትዮጵያ የተካሄደው ፖለቲካዊ ለውጥ ከአገሪቱ አልፎ የአፍሪካን መልካም ስም የሚገነባ መሆኑን የጀርመኑ ፕሬዚዳንት ፍራንክ ዎልተር ስቴይንሜዬር ተናገሩ።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ የጀርመኑን ፕሬዚዳንት ዛሬ በጽህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋግረዋል።

ፕሬዚዳንቱ ኢትዮጵያ በአህጉር ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ መድረክም ተፅእኖ መፍጠር የምትችልበት ደረጃ ላይ መሆኗን በዚሁ ጊዜ ተናግረዋል።

"ይህ ከኢትዮጵያ ጋር የነበረንን ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ የምናሳድግበት ትክክለኛው ወቅት ነው" ብለዋል።

ለውጡ በዴሞክራሲ ግንባታ ብቻ ሳይሆን በሴቶች ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተሳትፎ ተጫባጭ ለውጥ ያመጣ መሆኑ ደግሞ 'አገሪቷ እንደ ሞዴል እንድትታይ አድርጓታል' ነው ያሉት።

የአፍሪካ ፖለቲካ በዴሞክራሲ እጦት፣ በግጭት፣ በጦርነትና በሴቶች ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ ማነስ እንደሚኮነን ጠቅሰው ኢትዮጵያ ይህን ለውጥ ማድረጓ ከሚያመጣው ተጨባጭ ውጤት ባሻገር ለአህጉሪቷ መልካም ስም ግንባታ ትልቅ ሚና አለው ብለዋል። 

የፖለቲካ ለውጥ ትክክለኛውን መስመር እስኪይዝ የራሱ ፈተናዎች አሉት ያሉት ፕሬዚዳንቱ በተለይ የህዝቡን ፍላጎት ከማሟላትና ጥያቄውን ከመመለስ አንጻር የዴሞክራሲ ግንባታ በአንዴ የሚመለስ እንዳልሆነ አክለዋል።

ጀርመን በኢትዮጵያ ይህ እንዲሳካ ድጋፍ እንደምታደርግም ተናግረዋል።

በንግድና ኢንቨስትመንት ዘርፍም 'ኢትዮጵያ እስካሁን ከነበረው በበለጠ የግሉን ዘርፍ ማሳተፍ በምትፈልግበት ደረጃ ላይ መሆኗን ተረድቻለሁ' ነው ያሉት ፕሬዚዳንቱ።

በርካታ የጀርመን ኩባንያዎች ይህን ዕድል ለመጠቀም ፍላጎት እንዳላቸው በመግለጽ።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የጀርመኑ የመኪና አምራች ኩባንያ ቮልስ ዋገንን ጨምሮ ሌሎች ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ ኢትዮጵያ ለመምጣት በሂደት ላይ መሆናቸውንም ጠቁመዋል።

ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ በበኩላቸው የሁለቱ አገራት ግንኙነት የቆየና ውጤታማ መሆኑን ተናግረው የፕሬዚዳንቱ ጉብኝት ግንኙነቱን አሁን ካለው ለውጥ ጋር 'በአዲስ መልክ ለማጠናከር የሚረዳ ነው' ብለዋል።

ኢትዮጵያ ከጀርመን ጋር ብቻ ሳይሆን ከተባበሩት መንግስታት፣ ከአፍሪካ ዩኒየን፣ ከአውሮፓ ህብረትና ሌሎች ባለብዙ ግንኙነት ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ያላትን በጋራ የመስራት ልምድ አጠናክራ እንደምትቀጥልም ገልፀዋል።

በዚህ ረገድ በተለይ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣናና በሌሎች አካባቢዎች ሠላምና መረጋጋት በማስፈን ረገድ ጀርመን ትልቅ ሚና ስላላት በጋራ እንደሚሰሩም ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያና የጀርመን ግንኙነት በሁለቱ አገራት የጋራ ጥቅም ላይ እስከተመሰረተ ድረስ በፖለቲካ፣ በኢንቨስትመንት፣ በንግድና በሌሎችም መስኮች ገደብ የለውም ሲሉ ፕሬዚዳንቷ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም