የወጣቶችና ሴቶች ተጠቃሚነት እንዲጎለብት እንሰራለን - የብአዴን አመራሮች

65
አዲስ አበባ ግንቦት 19/2010 የብሄረ አማራ ዴሞክራሴያዊ ንቅናቄ (ብአዴን) አመራሮች የወጣቶችንና ሴቶችን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ በማሳደግ ተጠቃሚነታቸውን ለማጎልበት ከመቼውም ጊዜ በላይ ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋገጡ። ከክልል ውጭ በየደረጃው የሚገኙ  የብአዴን አመራሮች ኮንፍረንስ "የተሃድሶ ንቅናቄያችንን የበለጠ በማጥለቅ፣ በማስፋትና ቀጣይነቱን በማረጋገጥ የህዝባችንን የለውጥ ተስፋ እናስቀጥል" በሚል መሪ ሃሳብ ግንቦት 18 እና 19 ቀን 2010 ዓ.ም ተካሂዷል። በአዲስ አበባበ ሲካሄድ የነበረው የብአዴን አመራሮች ኮንፍረንስ ባለስምንት ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ተጠናቋል። ''የወጣቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ ለማሳደግ፣ ኢኮኖሚያዊ ጥያቄዎቻቸውን በራሳቸው ተሳትፎ ምላሽ ለመስጠትና ለማህበራዊ ጠንቆች ተጋላጭነታቸው እንዲቀንስ አጽንኦት ሰጥተን እንሰራለን'' ብለዋል። የክልሉን ሴቶችን ፖለቲካዊ ተሳትፎ በማሳደግ የውሳኔ ሰጪነት አቅማቸውን ለመጠቀም፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጥያቄዎቻቸውን ለምፍታት በትኩረት ለመስራት አመራሮቹ ከውሳኔ ላይ መድረሳቸውን በአቋማቸው ገልጸዋል። የአማራ ዴሞክራሲያዊ ብሄርተኝነትን ለማጎልበት ከመቼውም ጊዜ በላይ እንደሚሰሩ አመራሮቹ ከስምምነት ላይ ደርሰዋል። በጥልቅ ተሃድሶው የተለዩ የፌደራሊዝም ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥሉና ዴሞክራሲያዊ አንድነትን የሚፈታተኑ አስተሳሰቦችን ለማስተካከል እርምጃ ተጀምሯል። በዚህም የአማራ ብሄርተኝነት በዲሞክራሲያዊ ብሄርተኝነት ቅኝት እንዲጎለብት በየደረጃው ያሉ አመራሮች ስምምነት ላይ እንደደረሱ በመግለጫው ተመልክቷል። የክልሉ ዜጎች በህገ መንግስቱ መሰረት ሰብዓዊ መብታቸው ተጠብቆ ተዘዋውሮ መስራት እንዲችሉ ብአዴን ከአጋር ድርጅቶች ጋር ይሰራል ተብሏል። ከአማራ ክልል ውጭ ያሉ የክልሉ ተወላጆች በሚኖሩበት አካባቢ እንደማንኛውም ዜጋ እኩል ተከብረው እንዲኖሩ ለማድረግ አመራሮቹ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል። በአገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ስርዓት እንዲጎለብት ለተፎካካሪ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ መፍጠር፣ የዲሞክራሲ ተቋማትን ማጠናከር፣ የብዙሃን ማህበራት፣ ሚዲያዎችና የህዝብ ምክር ቤቶች እንዲጠናከሩ ይሰራል። በጥልቅ ተሃድሶው ወቅት የስርዓቱ አደጋ ተብለው የተለዩ ሙስናና ብልሹ አሰራር እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ለመመከት ይሰራል። በአገሪቱ የታየውን አንጻራዊ ሰላምና መረጋጋት ዘላቂነት እንዲኖረው ሰላምን የሚያውኩ የህግ የበላይነትን የሚጻረሩ ህገ ወጥ ደርጊቶችን ከኅብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ለማስቆም ተስማምተዋል።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም