ከባህር ዳር ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ የነበረ ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ተያዘ

103

አዲስ አበባ ጥር 20/2011 ከአማራ ክልል ባህር ዳር ከተማ ወደ አዲስ አበባ በህገ-ወጥ መንገድ ሲጓጓዝ የነበረ ሶሰት መትረየስና በርካታ ጥይቶች መያዙን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ ፡፡ 

በህዝብ ጥቆማ የተያዘው የጦር መሳሪያ የሰሌዳ ቁጥር ኮድ 3 አ/አ A- 59022 በሆነ ቶዮታ ፒካ አፕ ተሽከርካሪ ተፈታትቶ  ሲጓጓዝ  የነበረ ነው።

የፖሊስ ኮሚሽኑ ለኢዜአ እንደገለፀው ሦስት መትረየስ፣ 1924 የስታር እና 1856 የማካሮቭ የሽጉጥ ጥይቶች ከ37 የጥይት መያዥ ጋር ከሁለት ቀን በፊት የተያዘው በአዲስ አበባ ጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 1 ልዩ ቦታው አዲሱ ገበያ አከባቢ ነው።

የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን  ከህዝብ በደረሳቸው መረጃ መሰረት ባከናወኑት ተግባር ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያው በቁጥጥር ስር ውሏል። 

ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት የሚደረገው እንቅስቃሴ  ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ኮሚሽኑ አክሏል። 

ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመከላከል እየተከናወኑ ባሉ ስራዎች ህብረተሰቡ እያደረገ ያለውን ቀና ትብብር  ይበልጥ አጠናክሮ እንዲቀጥል የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽኑ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም