በሰሜን ሸዋ ዞን የተደራጁ ወጣቶች ምርታቸውን ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ ገቢ እያስገኙ ነው

70

ደብረ ብርሃን ጥር 20/2011 በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች የተደራጁ ወጣቶች ምርታቸውን ለውጪ ገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሬ  ማስገኘት መጀመራቸውን ተናገሩ።

ለ17 ኢንተርፕራይዞች በተፈጠረው የውጪ ገበያ ትስስርም 346 ሺህ 140 ዶላር የውጭ ምንዛሬ መገኘቱም ተገልጿል።

በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኘው "የኔነሽ ማሞ ልብስ ስፌት ኢንተርፕራይዝ" ስራ አስኪያጅ ወይዘሮ የኔነሽ ማሞ ለኢዜአ እንደገለጹት ሥራቸውን ከሁለት ዓመት በፊት በ3ሺህ ብር ካፒታል በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው የአልጋ ልብስና መጋረጃ በመስፋት እንደጀመሩ ገልጸዋል። 

በ120 ሺ ብር ስምንት የመስሪያ ማሽኖችን በብድር በመግዛት እንዲሁም ከደብረ ብርሃን ከተማ አስተዳደር በተደረገላቸው የማምረቻ ሼድ ድጋፍ በተደራጀ አግባብ ወደሥራ መግባት እንደቻሉ ተናግረዋል።

የሃገር ባህል ልብሶችን ሰርተው ለሃገር ውስጥና ለውጭ ሃገር ገበያ በማቅረብ ባደረጉት ጠንከራ እንቅስቃሴም በአጭር ጊዜ ውስጥ ካፒታላቸውን አንድ ሚሊዮን ብር ለማድረስ መቻላቸውን ገልጸዋል።

ስድስት በዘርፉ ለሰለጠኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን የተናገሩት ወይዘሮ የኔነሽ፣ በዚህ ዓመት ብቻ 92 ኪሎ ግራምየተዘጋጁየሃገር ባህል ልብሶችን እሴት ጨምረው በቦትስዋና እና በጅቡቲ በተካሄደ ዓለም አቀፍ የንግድ ትርኢትና ኤክፖ ላይ መሳተፋቸውን ገልጸዋል።

በዚህም ከ3 ሺህ የአሜሪካን ዶላር በላይ ትርፍ ማግኘት ከመቻላቸው በላይ ከአምስት ሃገራት ከመጡ ነጋዴዎች ጋር የገበያ ትስስር በመፍጠር በዘላቂነት ተወዳዳሪ የሆነ ምርት ለማቅረብ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን አስረድተዋል።

በእዚሁ ከተማ የ" ሶፊ ሸዋ ጋርመንት ኢንተርፕራይዝ " ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ  ሲፊያ መሐመድ በበኩላቸው "ቀደም ሲል በግል ተቀጥረው ሲሰሩ የእለት ወጪያቸውን ለመሸፈን እቸገር ነበር" ብለዋል።

ከሦስት ዓመት ወዲህ በሃገር ባህል ልብስ ዘርፍ በአነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ተደራጅተው ወደሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።

"ከመንግስት በተደረገላቸው የሼድ ድጋፍና ከዋልያ ካፒታል እቃ ፋይናስ አክስዮን ማህበር ባገኘሁት 150 ሺህ ብር ብድር ዘመናዊ ማሽን በማስገባት ጥራት ያላቸውን የባህል ልብሶች ለገበያ ማቅረብ ችያለሁ" ብለዋል።

ከጳጉሜን 2 እስከ መስከረም 3 ቀን 2011 በናይሮቢ ከተማ በተካሄደ "ኢንተርናሽናል ትሬድ ሴንተርና ኦሪጅን አፍሪካ የፋሽን ትሪኢትና ኢግዚቢሽን" ላይ በመሳተፍ ምርታቸውን ለዓለም ገበያ የማስተዋወቅ ዕድል ማግኘታቸውንም ተናግረዋል።

በእዚህም 220 ሺህ ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ከማግኘታቸው በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገራት ከመጡት ተሳታፊዎች ጋር የልምድ ልውውጥና የገበያ ትስስር መፍጠራቸውን አመልክተዋል።

በአሁኑ ወቅት የሀገር ባህል ልብሶችን ከሽመና እስከ ገበያ ድረስ ያለውን ሂደት በአንድ ማዕከል ለመስራት የሚያስችል አቅም መፍጠር እንደቻሉ ገልጸው፤ ወደ ውጭ ሃገር የጀመሩትን የገበያ ትስስርም አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

በዞኑ ቴክኒክ ሙያ ኢንተርፕራይዞች ልማት መምሪያ የውጪ ገበያ ልማት ባለሙያ አቶ ለማ ሀብተጊዮርጊስ በበኩላቸው ባለፉት ወራት በዞኑ ለ17 ኢንተርፕራይዞች የውጪ ሃገራት ገበያ ትስስር መፈጠሩን ገልጸዋል።

በእዚህም ኢንተርፕራይዞች ምርቶቻቸውን ለውጭ ገበያ ከማስተዋወቅ ባለፈ ለሀገሪቱ 346 ሺህ 140 ዶላር የውጭ ምንዛሬ ገቢ ማስገኘታቸውን አስታውቀዋል።

አቶ ለማ አንዳሉት የዘርፉን ተሳታፊዎች ቁጥር ለማሳደግም በቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች የሙያ ማሻሻያ ስልጠና ይሰጣል።

"በሀገር ውስጥ በተፈጠረ የገበያ ትስስርም 14ሺህ 780 አንቀሳቃሾችን ከባለሃብት፣ ከመንግስት ተቋማትና እርስ በእርስ በማገናኘት ከ215 ሚሊዮን ብር በላይ የገበያ ትስስር መፍጠር ተችሏል" ብለዋል።

በዞኑ ዘንድሮ 92 ሺህ 600 ሥራ ፈላጊዎችን አደራጅቶ ወደ ሥራ ለማሰማራት የታቀደ ሲሆን ባለፉት ስድስት ወራትም 26 ሺህ 600 ወጣቶችን በተለያዩ የገቢ ማስገኛ የስራ ዘርፎች ማሰማራት ተችሏል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም