ኢትዮጵያና ሱዳን በህዳሴ ግድብ ላይ ጠቃሚ ውይይት አድርገናል አሉ

3710

አዲስ አበባ ሚያዚያ 26/2010 ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድና ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ላይ ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ከፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ጋር ትናንት ማምሻውን በሱዳን ብሔራዊ ቤተ-መንግሥት የጋራ መግለጫ ሰጥተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ በዚሁ ጊዜ እንደተናገሩት፤ ከፕሬዚዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ጋር በሁለትዮሽና በቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ፍሬያማ ውይይት ተደርጓል።

በመጀመሪያም የአገራቱ የመንግሥታትና የሕዝብ ለሕዝብ ትስሰሩን የበለጠ ለማጠናከር በሚቻልባቸው ጉዳዮች ላይ ምክከር ማድረጋቸውን ገልጸዋል።

በተለይም በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት ማድረጋቸውን ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ የገለጹት።

የፕሮጀክቱን አሉታዊ ተጽዕኖ ለመቀነስ በኃላፊነት እየሰራን ነው፤ ግድቡንም በጋራ የምንገመግመው ይሆናል ነው ያሉት።

በምጣኔ ኃብት ረገድም አዲስ አበባና ካርቱምን በባቡር መስመር ለማስተሳሰር፣ የሱዳን ወደብን በጋራ ለማልማት፣ የንግድ የኢንቨስትመንት ልውውጡ እንዲጠናከር መስማማታቸውን ጠቁመዋል።

“የኢትዮጵያ ህዝብ ሱዳን ሲኖር፣ ኢትዮጵያ የኖረ ያህል ይሰማዋል፤ ለሱዳንም ተመሳሳይ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ ቁርኝት በሁለቱም በኩል መጠናከር አለበት ብለዋል።

አገራቱ በተለይም ካሏቸው ከፍተኛ የሕዝብ ቁጥር አንጻር ያላቸው ትስስር ለሌሎች አፍሪካ አገራት ምሳሌ እንደሚሆን ጠቁመዋል።

ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር በበኩላቸው ግድቡ የሦስቱን አገራት ጥቅም በማይጋፋ መልኩ የሚካሄድ ፕሮጀክት መሆኑንና በወሳኝ ነጥቦች ላይ የጋራ ምክክር ማድረጋቸውን ነው ያነሱት።

ግድቡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ቢሆንም ሱዳን በገንዘብም ጭምር ተሳታፊ የመሆን ፍላጎት እንዳላት ነው ፕሬዝዳንቱ የገለጹት።

ውይይታቸውም በግድቡ ውኃ አሞላል፣ ግድቡ ሊያስከትል በሚችለው የደህንነት ጉዳይና ሥራ ሲጀምር ለታችኛው ተፋሰስ አገራት በሚሰጠው ጥቅም ዙሪያ ማተኮሩን ጠቁመዋል።

በድንበር አካባቢ ነጻ የንግድ ቀጠና ለመፍጠርና የተሳለጠ የሎጂስቲክ አሰራር በሁለቱ አገራት ድንበር ኮሪደሮች ተግባራዊ እንዲሆን መስማማታቸውን ተናግረዋል።

የአገራቱን የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ለማጠናከር መሰራት እንዳለበት የገለጹት ፕሬዝዳንቱ በቀጣናዊ የሰላምና የደኅንነት ጉዳይ ላይም በጋራ ለመሥራት በሚያስችሉ መንገዶች ላይ መምከራቸውን አስረድተዋል።