የከተማዋ ጽዳትና የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ የተጠናከረ አለመሆኑ ተገለጸ

151

ጥር አዲስ አበባ 19/2011 ህብረተሰቡ ላይ  የተጠናከረ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ አለመሰራቱና የጽዳት ስራው ወጥነት የሌለው መሆኑን ተከትሎ  የከተማዋን ጽዳት ውጤታማ አለመሆኑን ኢዜአ ያነጋገራቸው የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ለነዋሪውን የግንዛቤ ማስጨበጥ ስራውን እያጠናከረና የጽዳት ሰራውንም እያዘመነ እንደሚገኝ ነው የተናገረው  ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪ  አቶ ሰለሞን አስቻለው እንደተናገሩት ህብረተሰቡ ጽዳት ለራስ ነው የሚለውን ባህል እንዲያዳብር የተሰራው ስራ ወጥነት የሌለው በመሆኑ የከተማው ጽዳት ውጤታማ አልሆነም ፡፡

በከተማው የሚከናወነው ጽዳት አብዛኛውን ግዜ በዘመቻ መልክ ሲካሄድ እንደሚታዘቡ ጠቅሰው፤ ይህን አሰራር መቀየርና  ነዋሪው ቀጣይነት ያለው የጽዳት ስራ እንዲከውን ማድረግ  ያስፈልጋል  ነው ያሉት ፡፡

"ለጥምቀት በአል እንደሚካሄደው የጎዳናዎች ጽዳት በከተማው በቋሚነት በየአካባቢው ሊካሄድ ይገባል"  የሚሉት አቶ ሰለሞን  ህብረተሰቡ የአካባቢውን ጽዳት የዘወትር ተግባሩ እንዲያደርግ የከተማ አስተዳደር በወጥነት  ግንዛቤ መፍጠር ይገባዋልም  ብለዋል ፡፡

ሌላው የከተማው ነዋሪ  ወይዘሮ አዲስ ደሳለኝ በአንድ ወቅት በከተማው ዋና ዋና መንገዶች የደረቅ ቆሻሻ መጣያዎች (ደስት ቢኖች) ተተክለው አገልግሎት ይሰጡ ነበር አሁን ግን አብዛኞቹ ተነቅለው ወይም ተበላሽተው ይገኛሉ ብለዋል ፡፡

 በየቤቱ የሚጠራቀሙ ቆሻሻዎች በወቅቱ አለመነሳታቸው  ጽዳቱ  ላይ ችግር እየፈጠሩ ይገኛሉ  ያሉት  ወይዘሮ አዲስ በአንዳንድ አካባቢዎች ቆሻሻዎች በቶሎ አለመነሳታቸው ሽታ ከማምጣታቸው በተጨማሪ የከተማው ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽህኖ እየፈጠሩ ይገኛሉም ሲሉ አስረድተዋል ፡፡

በህብረተሰቡ የቆሻሻ አያያዝና አወጋገድ ላይ ያለው የግንዛቤ ችግር በከተማው ጽዳትና በጤናቸው ሳይቀር ችግር እየፈጠረ እንደሚገኝ  የተናገሩት  ደግሞ በጽዳት ስራ ላይ የተሰማሩት ወይዘሮ አልማዝ ሞገስ  ናቸው ፡፡

አብዛኛው ህብረተሰብ ቆሻሻዎችን የሚበሰብሰውን ከማይበሰብሰው ሳይለይ አንድ ላይ አጠራቅሞ ማስወገዱ በከፍተኛ ሁኔታ የሚታይ ችግር መሆኑን  ወይዘሮ አልማዝ አመልክተዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የጽዳትና ደረቅ ቆሻሻ አገልግሎት ኤጀንሲ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ እሸቱ ለማ እንደተናገሩት ከተማው ጽዱና ውብ እንዲሆን የሚያስችሉ ለነዋሪው የግንዛቤ መፍጠርና ዘመናዊ የጽዳት አወጋገድ አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል፡፡

በከተማዋ ጎዳናዎች  አዳዲስ የደረቅ ቆሻሻ ደስት ቢኖች ፣ተጨማሪ ኮምፓከተሮችና በሞያው የሰለጠኑ የባለሞያዎችን ቁጥር በማሳደግ የቆሻሻ አወጋገዱን  ለማዘመን እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡

የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ከሚሰራው የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራዎች በተጨማሪ በአሁኑ ወቅት ከ1000 ትምህርት ቤቶች  ጋር በመቀናጀት ቆሻሻ የሚጠየፍ ትውልድ ለመፍጠር  እየተሰራ ነው ሲሉም አመልክተዋል ፡፡

የህብረተሰቡን ግንዛቤም ለማሳደግ ከጥቅምት ጀምሮ በየወረዳው የባለሙያዎች ቁጥርን ከ3 ወደ 9  በማሳደግ  በየቀጠናው  እየገቡ የቁሻሻ አወጋገድና ሌሎች የጽዳት ጉዳዮች በተመለከተ በርካታ ስራ እየሰሩ ይገኛሉ ብለዋል፡፡

በየቤቱ የሚሰበሰብ ቆሻሻ በግዜው የማይነሳበት ሁኔታ በአንዳንድ ቦታ ይታያል እንዲሁም ግዚያዊ የቆሻሻ መሰብሰቢያ እጥረትና ቆሻሻ  በ24 ሰዓት የማይነሱበት ሁኔታ እንዳለ ያመለከቱት ሰራ አስኪያጁ  ችግሩን ለመቅረፍ በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም አመልክተዋል ፡፡

ቆሻሻ በግዚያዊነት  ከሚጠራቀሙበት ቦታ በየ24 ሰዓቱ ለማንሳት በሚደረገው ጥረት የኮምፓክተሮች ቁጥር አናሳ መሆንና የመበላሸት ችግር ቆሻሻ ወደ ማስወገጃ ቦታ በተፈለገው ሰዓት ማድረስ እንዳላስቻለ የተናገሩት ስራ አስኪያጁ  50 አዳዲስ  ኮምፓክተሮች ለመግዛት የሰላሳ በመቶ ክፍያ ተፈጽሟል  ብለዋል

በከተማው የሚገኙ በጎዳናዎች ላይ የተተከሉ የደረቅ ቆሻሻ መጣያወገጃ (ደስት ቢን ) ያረጁ መሆናቸውን ከዚህ ወር ጀምሮ በዘመናዊ የደስት ቢን የመቀየር ስራ ለመስራት ዝግጅት ተጠናቆልም ሲሉ ስራ አስኪያጁ አስረድተዋል፡፡

ቆሻሻ ሀብት ነው ያሉት ስራ አስኪያጁ በበጀት አመቱ 6 ወራት ብቻ ቆሻሻ በመለየት የተሰማሩ ማህበራት  ብቻ 49  ሚሊዮን ብር ከዘርፉ   ተጠቃሚ መሆን መቻላቸውን አስገንዝበዋል ፡፡

የጽዳት ሰራ ውጤታማ የሚሆነው ህብረተሰቡ ጊቢውን ብቻ ሳይሆን አካባቢውን ብሎም  ከተማውም በማጽዳት በኩል ሲሳተፍና ሃላፊነቱን በአግባቡ ሲወጣ በመሆኑ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል  የኔነት ስሜቱን ሊያጠናክር ይገባል ብለዋል፡፡

ሚዲያዎች የጽዳት ስራውን በተፈለገው ደረጃ እያገዙ እንዳልሆነ የጠቆሙት ስራ አስኪያጁ ለጽዳጽ ስራው ውጤታማነቱ ከአስተዳደሩ ጋር በጋራ መስራት እንደሚገባቸውም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፤

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም