ወጣቶች የመቻቻል ባህልን እንዲያዳብሩ ኃላፊነታችንን እንወጣለን...በጅግጅጋ የሰላም ኮንፈረንስ ተሳታፊዎች

81

ጅግጅጋ  ጥር 18/2011 ወጣቶች እርስ በርስ የመቻቻል ባህልን እንዲያዳብሩ ኃላፊነታችንን እንወጣለን ሲሉ በጅግጅጋ ከተማ በተካሄደ የሰላም ኮንፈረንስ ላይ የተሳተፉ ሴቶች ገለጹ።

" ብዝሃነት፣ መቻቻልና እርቅ ለሀገራዊ አንድነት ግንባታ መሰረት ነው " በሚል ክልል አቀፍ የሴቶች የሰላም ኮንፈረስ ትላንት በጅግጅጋ ከተማ  ተካሂዷል።

የክልሉ ሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ባዘጋጀው  መድረክ ላይ ከክልሉ 93 ወረዳዎች እና 6 የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሴቶች አደረጃጀትና የነዋሪዎች ተወካዮች የተገኙ ሲሆን ለውይይት መነሻ ጹሁፍ ቀርቦም ውይይት ተደርጎበታል።

በመድረኩ ከተሳተፉት ሴቶች መካከል የሺኒሌ ወረዳ የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ፋጡማ አብዲ እንዳሉት ለህብረተሰቡ በተለይ ለወጣቶች የሰላምን ጥቅም ለማስተማር መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

"የሰላምን ዋጋ ታች ህብረተሰቡ ድረስ ወርደን ከማስተማር ባለፈ ወጣቶች በማህበራዊ ሚዲያ በሚያገኙት አሉባልታ ተነሳስተው ያልተገባ ተግባር እንዳይፈጽሙ በንቃት እንሰራለን" ሲሉም ገልጸዋል።

ሴቶች የህብረተሰቡ የጀርባ አጥንት መሆናችውን ጠቁመው በመድረኩ ያገኙትን እውቀት ለህዝቡ በማድረስና በመተግበር የአካባቢያቸውን ሰላም በተሻለ ሁኔታ ለማስጠበቅ እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

የሶማሌ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የሴቶችና የሕጻናት ጉዳይ ክፍል ኃላፊ ዋና ኢንስፒክተር ፈርሂያ አብዲራህማን እንዳሉት በተለያዩ ምክንያቶች በክልሉ በተነሱ ግጭቶችና አለመረጋጋቶች ሴቶችና ህፃናት ዋነኛው ተጠቂ ናቸው።

የክልሉ ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ዘይነብ ሀጂ አደን በበኩላቸው ፎረሙ ሴቶች ሰላምን ለማረጋገጥ ያላቸውን ሚና ለማጎልበት ያለመ የመጀመሪያ የሰላም ኮንፈራንስ መሆኑን ገልጸዋል።

ዋና ኢንስፒክተር ፈርሂያ እንዳሉት እናቶች ልጆቻቸውና ባሎቻቸውን በመከታተል ሰላምን የሚያናጉ አላስፈላጊ ተግባራት ላይ እንዳይሰማሩ ማድረግ ይጠብቅባቸዋል።

ቢሮ የክልሉ ህዝብ በተለይ ወጣቶች ከጥላቻ ይልቅ እርስ በርስ የመቻቻል ባህልን እንዲያዳብሩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ተናግረዋል።

"በክልሉ በዋናነት የጸጥታ ችግር እያስነሱ ያሉት ወንዶች ናቸው" ያሉት ወይዘሮ ዘይነብ ሴቶችም ከጃርባ ሆኖ በማበረታታት ተሳትፎ እያደረጉ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከክልሉ 93 ወረዳዎች እና ስድስት የከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የሴቶች አደረጃጀትና የነዋሪዎች ተወካዮች በኮንፈራንሱ ማጠቃለያ ላይ ባለአምሰት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተዋል።

በአቋም መግለጫውም በሀገሪቱና በክልሉ የተጀመረውን ለውጥ ለማጠናከር፣ የህብረተሰቡን ሰላም ለመጠበቅ፣ ወጣቶችን ለማስተማር፣ ጎሰኝነትን ለመታገልና የህብረተሰቡን አንድነት ለማጠናከር አጠብቀው እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።

ኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከቶችን ከመታገል ባለፈ በማህበረሰቡ ውስጥ የነበረውን የመቻቻል ባህል ወጣቱ እንዲያዳብረው ለማስተማርና ለክልሉ ሰላም ጠንክረው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

በክልሉ የሚሾሙ አመራሮች የሴቶችን እኩል የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲያረጋግጡና ለህዝቡ ያለአድሎ በትክክል እንዲሰሩ ከጎናቸው በመቆም ድጋፍ እንደሚያደርጉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም