በአሶሳና መተከል ዞኖች የዘንድሮ የትምህርት አፈጻጸም ደካማ መሆኑ ተጠቆመ

1233

አሶሳ ጥር 18/2011 በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል አሶሳና መተከል ዞኖች የተያዘው ዓመት የትምህርት አፈጻጸም ደካማ መሆኑን የክልሉ ትምህርት ቢሮ አስታወቀ፡፡

የክልሉ ትምህርት ዘርፍ አፈጻጸም ግምገማ ትናንት በአሶሳ ከተማ ተጀምሯል፡፡

በእዚህ ወቅት የክልሉ ትምህርት ቢሮ የመረጃ ሥርዓትና ሃብት ማፈላለግ ባለሙያ አቶ ጠብቀው ወርቁ እንደተናገሩት በክልሉ አሶሳና መተከል ዞኖች ያለፉት ሦስት ወራት የትምህርት አፈጻጸምን ለመገምገም የመስክ ምልከታ ተደርጓል፡፡

የመስክ ግምገማው በዞኖቹ 13 ወረዳዎች በሚገኙ 52 አንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች ላይ ያተኮረ ነው፡፡

ውጤቱም ትምህርት ቤቶቹን ከሚመሩ የወረዳ ጽህፈት ቤቶች እስካሁን ድረስ ዕቅድ ያላዘጋጁ መኖራቸውንና ያዘጋጁትም ቢሆን እቅዳቸውን ተግባራዊ እንዳላደረጉ መረጋገጡን ገልጸዋል፡፡

በትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራም የተከናወኑ ተግባራት ቢኖሩም ህብረተሰቡን ለማሳተፍ የተደረገው ጥረት አነስተኛ በመሆኑ ግብአት በወቅቱ እየቀረበ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡

እንደባለሙያው ገለጻ ዘንድሮ በአንዳንድ ትምህርት ቤቶች በኦሮምኛ የአፍ መፍቻ ቋንቋ ትምህርት ቢጀመርም አመራሩ በቂ ድጋፍ እያደረገ አይደለም ፡፡

የልዩ ፍላጎት እና የጎልማሶች ትምህርት አሰጣጥም አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን ነው የተናገሩት፡፡

“ዘንድሮ ትምህርት በሁሉም ትምህርት ቤቶች ወጥ በሆነ መንገድ አለመጀመሩም ትምህርት የሚያቋርጡ ተማሪዎች ቁጥር እንዲጨምር ምክንያት ሆኗል” ብለዋል፡፡

በህብረተሰቡ ተሳትፎ ከተሰሩ ትምህርት ቤቶች አንዳንዶቹ ተገቢውን እንክብካቤ ባለመኖሩ እየፈራረሱ መሆኑንም አስታውቀዋል፡፡

አንደባለሙያው ገለጻ የመምህራን ደረጃ እድገት፣ ቅጥርና ዝውውር ፍትሃዊነት የጎደለው ከመሆኑም በላይ መምህራን የመኖሪያ ቤት ቦታ እንዲያገኙ በመመሪያ ቢፈቀድም እስካሁን አልተተገበረም፡፡

ኢዜአ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስ ኩዊ በበኩላቸው ቢሮው የተጠቀሱ ችግሮችን ለመፍታት የ100 ቀናት እቅድ ተዘጋጅቶ ወደሥራ ሊገባ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በእቅዱ የመምህራን ጥቅማ ጥቅም ጉዳይ ዋነኛ ትኩረት የተሰጠው መሆኑንም ኃላፊው አመልክተዋል፡፡

“በተለይም የትምህርት አመራሩን በጠንካራ ክትትልና ግምገማ ወደ ሥራ ማስገባት የዕቅዱ ዋነኛ ማስፈጸሚያ አቅጣጫ ነው” ብለዋል፡፡

ለሦስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው በእዚህ የትምህርት አፈጻጸም ግምገማ የዞንና የወረዳ የትምህርት አመራሮችና ባለሙያዎች እየተሳተፉ ነው ነው፡፡