በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱ የቀድሞ የሜቴክ የስራ ኃላፊዎች ላይ የክስ መቃወሚያ ቀረበ

54

አዲስ አበባ ጥር 17/2011 በከባድ የሙስና ወንጀል የተከሰሱት የብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) የቀድሞ የስራ ኃላፊዎች ላይ የክስ መቃወሚያ ቀረበ።

በዚህ መዝገብ የተከሰሱት ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኝው፣ ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ፣ ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ፣ ኮሎኔል ጌትነት ጉደያ /ያልተያዙ/፣ ኮሎኔል ጉይቶም ከበደ /ያልተያዙ/፣ አቶ ቸርነት ዳና፣ ኢሌኒ አብርሃና /ያልተያዙ/፣  አቶ ረመዳን ሙሳ ሲሆኑ ጥር 2 ቀን 2011 ዓ.ም በአቃቤ ሕግ ክስ ቀርቦባቸዋል።

ተከሳሾቹ በሜቴክ ሥር ለሚገኘው የአዳማ እርሻ መሣሪያዎች ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ አገልግሎት የሚውሉ ትራክተሮች ግዥ በተካሔደበት ወቅት፣ ከኮርፖሬሽኑ የግዥ አፈጻጸም መመሪያ ውጪ ያለጨረታ ግዢ እንዲፈጸም በማድረግ ወንጀል እንደተከሰሱ ተገልጿል።

በዛሬው እለትም ብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ፣ አቶ ቸርነት ዳና እንዲሁም አቶ ረመዳን ሙሳ የክስ መቃወሚያቸውን ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 15ኛ ወንጀል ችሎት በጠበቆቻቸው በኩል በጽሑፍ  አቅርበዋል።

ነገር ግን የሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘው ጠበቃ ባለመገኘቱ፤ የኮሎኔል ደሴ ዘለቀ ጠበቃ የደንበኛቸው የክስ ትርጉም ተሟልቶ ባለመቅረቡ መቃወሚያቸውን ለችሎቱ ሊያቀርቡ እንዳልቻሉ አስረድተዋል።

በዚሁ መዝገብ የተከሰሱትና ያልተያዙት 4ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል ጌትነት ጉደያ፣ 7ኛ ተከሳሽ ኢሌኒ አብርሃ ለስራ ወደውጭ ሔደው እንዳልተመለሱ ዐቃቤ ሕግ ለፍርድ ቤቱ ያመለከተ ሲሆን 5ኛ ተከሳሽ ኮሎኔል ጎይቶም ከበደ ሊገኙ አልቻሉም።

ፍርድ ቤቱ ሜጀር ጀኔራል ክንፈ ዳኘውና ኮሎኔል ደሴ ዘለቀ በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ የክስ መቃወሚያቸውን አዘጋጅተው ለጥር 24 ቀን 2011 ዓ.ም እንዲያቀርቡ ትእዛዝ ሰጥቷል።

በተጨማሪም የክስ መቃወሚያ ያቀረቡትን የብርጋዴር ጀኔራል ጠና ቁርንዲ፣ አቶ ቸርነት ዳናና አቶ ረመዳን ሙሳ ጉዳይን ለማየትም ለጥር 30 ቀን 2011 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ ይዟል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም