የመጀመሪያው የመገናኛ ብዙሃን አውደ ርዕይ -መገናኛ ብዙሃንን በአንድ ቦታ እንዲገናኙ ያደረገው መድረክ

98

አዲስ አበባ ጥር 17/2011 በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙኃን አውደ ርዕይ ዛሬ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ተከፈተ።

በ”ኦን ፕሮሞሽን” የተዘጋጀው አውደ ርዕይ በመገናኛ ብዙኃን መካከል የቴክኖሎጂና የልምድ ልውውጥ እንዲኖር ያግዛልም ተብሏል።

በአውደ ርዕዩ የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ኤጀንሲን ጨምሮ በቴሌቪዥን፣ በሬዲዮ፣ በህትመትና ዲጀታል ሚዲያ ስራ ላይ ከ70 በላይ የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት እና ሌሎች ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ተያያዥነት ያላቸው ስራዎችን የሚያከናውኑ ድርጅቶች የተሳፉበት ነው።

ኢዜአ በአውደ ርዕዩ መክፈቻ ላይ በመገኘት ተሳታፊዎችን የአውደ ርዕዩ መዘጋጀት ስለሚኖረው ፋይዳ አነጋግሯል።

የመገናኛ ብዙሃን አውደ ርዕዩ በመገናኛ ብዙሃን መካከል የእርስ በእርስ መማማርና የተከታይ እድል ለማስፋት በር ከፋች እንደሆነ ነው የአውደ ርዕዩ ተሳታፊዎች የሚገልጹት።

በአውደ ርዕዩ ላይ ተሳታፊ ከሆኑት መካከል ሻምፒዮንስ ኮሙኒኬሽን አንዱ ሲሆን ድርጅቱ በየወሩ የሚወጣውን የኢትዮጵያ ቢዝነስ ሪቪው መጽሔትና በየሳምንቱ የሚወጣው አዲስ ማለዳ ጋዜጣን ያሳትማል።

የሻምፒዮንስ ኮሙኒኬሽን የገበያ ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉጌታ ተሰማ ከዚህ በፊት እንዲህ አይነት መድረኮች አለመኖራቸው መገናኛ ብዙሃን እርስ በእርሳቸው ልምድ እንዳይለዋወጡ በማድረግ ረገድ ጉዳት እንደነበረው አንስተዋል።

በተበታተነና በግል ጥረት መገናኛ ብዙሃን የሚያደርጉት ግንኙነት ውጤታማ እንዳልነበረና ይህ አውደ ርዕይ መዘጋጀቱ መገናኛ ብዙሃንን በአንድ ቦታ ተገናኝተው እርስ በእርስ ያላቸውን አገልግሎት እነዲያስተዋዉቁና ለመማማር እንደ መንደርደሪያ እንደሚያግዝ ገልጸዋል።

ከዚህ በተጨማሪም መገናኛ ብዙሃን ከደንበኞቻቸው ጋር በመገናኛት ማን ምን ይፈልጋል? ከሚለው የሚለውን ለመለየትም እድል እንደሚፈጥርላቸው ተናግረዋል።

የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት የብራንዲግና የሁነት ዝግጅት ምክትል ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ክንዱ በበኩላቸው አውደ ርዕዩ መገናኛ ብዙሃን እርስ በእርስ ተነጋገረው በቀጣይ ጠንካራ ግንኙነት እንዲኖራቸው ለማድረግ በር ይከፍታል ብለዋል።

መገናኛ ብዙሃን ጊዜው የደረሰበትን ቴክኖሎጂ ከመጠቀምና የአሰራር ስርዓታቸው ምን ደረጃ ላይ ደርሰዋል? ከሚለው ነገር አንጻርም አውደ ርዕዩ መገናኛ ብዙሃን ልምድ እንዲለዋወጡ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

መገናኛ ብዙኃንን በአንድ መድረክ ያገናኘው አውደ ርዕይ ዘላቂነት ሊቀጥል እንደሚገባና መገናኛ ብዙሃን እርስ በእርስ መማማርን ለመለማመድ የሚያስችል መድረክ መፍጠር እንዳለባቸውም አመልክተዋል።

የብስራት ፕሮሞሽን የዋና ስራ አስኪያጅ ረዳት ወይዘሮ ቤተልሄም ጌታቸው ድርጅታቸው በአካል ጉዳተኞች ላይ ያተኮሩ ፕሮግራሞችን በመገናኛ ብዙሃን እንደሚያስተላልፍ ገልጸው የአውደ ርዕዩ መዘጋጀት መሰል ማህበራዊ ጉዳዮች ጋር ከሚሰሩ ተቋማት ጋር ለመተወዋቅ ይረዳልም ብለዋል።

እንዲህ አይነት መገናኛ ብዙሃንን የሚያገናኝ አውድ ርዕይ መዘጋጀቱ መገናኛ ብዙሃንና ሌሎች ተያያዥ ስራዎችን የሚሰሩ ተቋማት ተቀራርበው እንዲሰሩ እንደሚያደርግም ገልጸዋል።

በ”ኦን ፕሮሞሽን” የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙሃን አውደ ርዕይ አስተባባሪ አቶ ቴዎፍሎስ መኮንን አውድ ርዕዩ የተዘጋጀው መገናኛ ብዙሃን በእንድ መድረክ ተገናኝተው ልምድ እንዲለዋወጡና ጤናማ ግንኙነት እንዲኖራቸው በማሰብ እንደሆነ ገልጸዋል።

በ2012 ዓ.ም በሚካሄደው አውደ ርዕይ ከአውሮፓ፣ አፍሪካ፣ መካከለኛው ምስራቅና እስያም ጭምር መገናኛ ብዙሃን እንዲሳተፉ ለማድረግ እቅድ መያዙንና መገናኛ ብዙሃኑ ወደዚህ መጥተው በእውቀትና በቴክኖሎጂ ያላቸውን ልምድና ተሞክሮ እንዲያካፍሉ እንደሚደረግም ጠቅሰዋል።

የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር አቶ ገብረጊዮርጊስ አብርሃ በአውደ ርዕዩ የሚሳተፉት መገናኛ ብዙሃን አውደ ርዕዩ የተዘጋጀበትን ዓላማ ከግምት ውስጥ አስገብተው ተጨባጭ ውጤት የሚያመጣ የልምድ ልውውጥ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

መንግስትም በኢትዮጵያ የመገናኛ ብዙሃን እድገት እንዲመጣ ፍላጎት ካላቸው ተቋማት ጋር በአጋርነት እንደሚሰራና አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አመልክተዋል።

በኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የተዘጋጀው የመገናኛ ብዙኃን አውደ ርዕይ እስከ እሁድ ጥር 19 ቀን 2011 ዓ.ም ይቆያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም