ለጊኒዎርም በሽታ በተጋለጡ የገጠር ቀበሌዎች የውሃ ተቋማትን የማዳረሱ ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡-አቶ ኡሞድ ኡጁሉ

75

ጋምቤላ ጥር 17/2011 በጋምቤላ ክልል በንጹህ መጠጥ ውሃ እጦት ለጊኒዎርም በሽታ በተጋለጡ የገጠር ቀበሌዎች የውሃ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ።

በክልሉ ጎግ ወረዳ በጊኒዎርም በሽታ ተጋላጭነቱ በሚታወቀው የአቴቲ ቀበሌ የተገነባው የንጹህ መጠጥ ውሃ ተቋም ትናንት ተመርቆ አገልገሎት መስጠት ጀምራል።

ርዕሰ መስተዳደር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ የውሃ ተቋሙን በመረቁበት ወቅት እንዳሉት የውሃ ተቋማትን ተዳራሽ በማድረግ የህዝብን የንጹህ መጠጥ ውሃና የበሽታ ተጋለጭነት ችግር ለመፍታት እየተሰራ ነው።

"ባለፉት ዓመታት በሁሉም የገጠር ቀበሌሎች የውሃ ተቋማትን ተደራሽ በማደርግ የህዝቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለማቃለል ጥረት ቢደረግም የተፈለገውን ውጤት ማገኘት አልተቻለም" ብለዋል።

በመሆኑም የክልሉ መንግስት ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በተለይም ለጊኒዎርም በሽታ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የተለየ ትኩረት ሰጥቶ የውሃ ተቋማትን የማስፋት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።

በዕለቱ የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት የውሃ ተቋማትን ተደራሽ ለማድረግና የጊኒዎርምን በሽታው ለመከላከል እየተደረገ ላለው ጥረት አንድ ማሳያ መሆኑንም ገልጸዋል።

የተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ለውሃ ተቋሙ ግንባታ ላደረገው የ5 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር ድጋፍ ምስጋናቸውን ያቀረቡት አቶ ኡሞድ በቀጣይም ሌሎች ባለድርሻ አካላት ድጋፍና ትብብራቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ኡማን አሙሉ በበኩላቸው " ህብረተሰቡ በጊኒዎርም በሽታ እየተጠቃ ያለው የንጹው መጠጥ ውሃ አገልገሎት በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ ባለመሆኑ ነው " ብለዋል።

በመሆኑም በሽታውን ለማጠፋት በሚደረገው ጥረት የውሃ ተቋማትን የማስፋቱ ሥራ መጠናከር እንዳለበት ጠቁመው በዕለቱ የተመረቀው የውሃ ተቋም በቀበሌው የነበረውን የከፋ ችግር እንደሚፈታ ተናግረዋል።

"በክልሉ በገጠርና በከተማ የውሃ ተቋማትን በማስፋፋት የህዝቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር ለመፍታት በትኩረት እየተሰራ ነው" ያሉት ደግሞ የክልሉ ውሃና መስኖ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ቶክ ቾት ናቸው።

በአሁኑ ወቅት በተለይም ለጊኒዎርም በሽታ ተጋለጭ በሆኑ የገጠር ቀቤለዎች በርከታ የውሃ ተቋማት በመገንባት ላይ መሆናቸውንና በበጀት ዓመቱም የክልሉን ውሃ ሽፋን አሁን ካለበት 66 ከመቶ ወደ 89 ከመቶ ለማድረስ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በዕለቱ ተመርቆ ለአገልገሎት የበቃው የውሃ ተቋም በተደጋጋሚ ለጊኒዎርም በሽታ ሲጋለጡ የነበሩትን የአቴቲ ቀበሌ ነዋሪዎች ችግር እንደሚፈታ የጠቆሙት አቶ ቶክ፣ የውሃ ተቋሙ 1 ሺህ 640 ቤተሰቦችን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ከታደሙት የአቴቴ ቀበሌ ነዋሪዎች መካከል ወይዘሮ ኖች አበላ በሰጡት አስተያየት ቀደም ሲል በአካባቢው ከፍተኛ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር እንደበረ ገልጸዋል።

" የውሃ ችግር በመኖሩ ምክንያት የኩሬ ውሃ ስንጠቀም ለጊኒዎርምና ሌሎች የውሃ ወለድ በሽታ እንዳረግ ነበር፤ አሁን ግን ይህ የውሃ ተቋም በመሰራቱ ከችግሩ ተላቀናል "  ብለዋል፡፡

በንጹህ መጠጥ ውሃ እጦት ምክንያት ለከፈተኛ ችግርና እንግልት ተዳርገው መቆየታቸውን የገለጹት ደግሞ የእዚሁ ቀበሌ ነዋሪ አቶ አባለ አቻላ ናቸው።

አቶ አባለ ''ቀደም ሲል በአካባቢያችን የውሃ ተቋም ባለመኖር ውሃ ፍላጋ ስንገላታ ነበር ፣ አሁን ግን ይህ የውሃ ተቋም በመሰራቱ ችግር ተፈቶልናል፣ እውነትም መንግስት መኖሩን ማረጋገጥ ችለናል''  ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም