በትግራይ ክልል የዕጣን ተክልን ከጥፋት ለመታደግ እየተሰራ ነው

134

መቀሌ ጥር 17/2011 በትግራይ እየተመናመነ የመጣውን የዕጣን ተክል ከጥፋት ለመታደግ በምርምር የታገዘ ልማትና የጥበቃ ስራ እየተካሄደ መሆኑን የክልሉ ግብርናና ገጠር ልማት ቢሮ ገለጸ።

የእጣን ተክሉ በህገ ወጥ የእርሻ መስፋፋት፣በምንጣሮ፣ በእሳት ቃጠሎ ፣ ስርዓት በጎደለው የዕጣን  ለቀማ  ምክንያት ነው እየተመናመነ የመጣው፡፡

በቢሮው የደን ጥበቃና ቁጥጥር ባለሙያ አቶ ሙዑዝ ኃይሉ ለኢዜአ እንዳሉት በክልሉ በ1992 ዓ.ም.ተደርጎ በነበረው ጥናት የእጣን ዛፉ ከወርዒ በረሃ እስከ ተከዘ ወንዝ ጫፍ ድረስ ከ147ሺህ 600 ሄክታር በላይ ያካለለ ነበር።

በ2005ዓ.ም. በባለሙያዎች በተደረገው ጥናት ወደ 72ሺህ 292 ሄክታር ዝቅ ማለቱ ተረጋግጧል፡፡

ከዚሁ ስፍራ በዓመት ከ92ሺህ ኩንታል በላይ የዕጣን ምርት ይሰበሰብ የነበረው ደግሞ ከ40 ሺህ ኩንታል የማይበልጥ ሆኗል፡፡

ዕጣን በማምረት ስራ ተሰማርተው ተጠቃሚ የሆኑ ከ110 በላይ ማህበራትና ተቋማት ቢኖሩም ገቢ ከመሰብሰብ ባለፈ ተክሉን ለመንከባከብና ለመተካት የሚያደርጉት ጥረት ባለመኖሩ ሌለው ችግር ነው፡፡

የጠፋውን የዕጣን ዛፍ ለመተካትና ለማራባት በችግኝና  ቆርጦ በመትከል ለማስፋፋት ከዩኒቨርሲቲዎችና ከግብርና ምርምር በጋራ በጥናት የታገዘ ልማት እየተካሄደ መሆኑን ባለሙያው ገልጸዋል፡፡

"ተክሉ እንዲያገግም ለማድረግ ለሶስት ዓመት ጥቅም ላይ ሳይውል ነጻ እንዲሆን በማምረት ስራ የተሰማሩት ማህበራትና ተቋማት ከማምረት እንዲታቀቡ ተደርጓል "ብለዋል።

የዕጣን ዛፉ ባለባቸው አካባቢዎች ዙሪያውና ይዞታው የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።

በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የባዮ ቴክኖሎጂ ባለሙያ ረዳት ፕሮፌሰር ሓጎስ መሓመድ በበኩላቸው፣የዕጣን ዛፍ ከመጥፋት ለመታደግ በዘርና በቁርጥራጭ ለማራባት በቤተ ሙከራ ምርምር እያደረጉ መሆናቸውን ተናግረዋል።

"የተገኘው ውጤት በመገምገም በግሪን ሃውስ በ(መጠለያ  ውስጥ ሰርቶ ማሳያ) ሙከራና በመስክ ላይ ክትትል በማድረግ የሚያድግበት ዘዴዎች ለይተን ለማራባት እየሰራን ነው" ብለዋል።

የዕጣን ዛፍ ከጥፋት ለመከላከል ወጣቶች በማደራጀት ተንከባክበው እንዲያለሙትና እንደጠብቁት  ሰልጥነው እንደሚሰማሩ የገለጹት ደግሞ በምዕራባዊ ዞን ግብርናና ገጠር ልማት ጽህፈት ቤት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ቡድን መሪ አቶ ተስፋዬ ፀሐዬ  ናቸው።

"ከ10ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው ደግሞ የዕጣን ዛፍ ወደ ፓርክ አስገብተን ከሰውና እንስሳት ንክኪ ነፃ ሆኖ ከጥፋት እንዲጠበቅ አድርገናል" ብለዋል።

ቡድን መሪ እንዳሉት ተክሉ እየወደቀ እንዳይጠፋ ደግሞ በአጠገቡ ያሉ ተደጋጋፊና ተመጋጋቢ  ዛፎች እንዳይቆረጡ ለመንከበባከብና ለመጠበቅ ሰራተኞን በመቅጠር ጭምር እየተሰራ ነው።

ከዕጣን ተክል የሚገኘው ጥሬ ምርት  ለመድኃኒት፣ ለመስታዋት፣ ለሽቶ ፣ ለቀለምና ለሌላም ኬሚካል መስሪያ በግብአትነት የሚያገለግል  ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም