በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ ፍርድ ቤት ቀረቡ

67

ባህርዳር ጥር 17/2011 የጥረት ኮርፖሬት የቀድሞ ከፍተኛ አመራሮች አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደሰ ካሳ በተጠረጠሩበት የሙስና ወንጀል ዛሬ ባህር ዳርና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው ጉዳያቸው መታየት ጀመረ።

የቀረቡበት 2ኛ ወንጀል ችሎት የምርመራ መዝገቡን አጠናከሮ ለማቅረብ ለየካቲት 1/2011 የ14 ቀን የጊዜ ቀጠሮ ተሰጥቷል።

አቶ በረከት ስምኦን ስለተከሰሱበት ጉዳይ ለችሎቱ እንዳስረዱት በዳሽን ቢራ ፋብሪካም ሆነ በሌሎች የጥረት ኮርፖሬት ካምፓኒዎች ጠፍቷል ለተባለው ገንዘብ የዋስትና መብታቸው ተከብሮ በውጭ ሆነው ለመከራከር ፍርድ ቤቱ እንዲፈቅድላቸው ጠይቀዋል።

በአካባቢው የጸጥታ ሁኔታ ለህይወታቸው ስለሚሰጉ፣የቤተሰቦቻቸው አዲስ አበባ መኖርና በጤና ችግሮቻቸው ምክንያትም ያገኙትን ምግብ ስለማይመገቡ ጉዳያቸው አዲስ አበባ እንዲታይ ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

ፍርድ ቤት ከመቅረባቸው በፊትም በመገናኛ ብዙሃን የስም ማጥፋት እንደተካሔደባቸው ለቤቱ አስረድተዋል።

አቶ ታደሰ ካሳ በተመሳሳይ በጤና ችግሮቻቸው ምክንያት እንደልብ ስለማይመገቡ ቤተሰቦቻቸው በሚገኙበት አዲስ አበባ ጉዳያቸው እንዲታይ ጠይቀው 90በመቶ መረጃ እንደተሰበሰበ በመገናኛ ብዙሃን ሳይቀር በመገለጹ በውጭ ሆነው እንዲከራከሩ እንዲፈቀድላቸውም አመልክተዋል።

የቀረበው ክስም ቀደም ሲል በከፍተኛ አመራሩ፣ በቦርዱና በተቋሙ ሲገመገም የቆየና የሚታወቅ እንደሆነ ገልጸው በመገናኛ ብዙሃን በተለያዩ መንገዶች የስም ማጥፋት እንደተካሔደባቸው ተናግረዋል።

አቃቢ ህግ በበኩሉ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ከፍተኛ የገንዘብ መጠን በመሆኑና የቀደመ ስልጣናቸውን በመጠቀም ሰነድ ሊያጠፉ ይችላሉ ተብለው ስለሚጠረጠሩ ዋስትናው እንዳይሰጥ ተከራክሯል።

እንዲሁም ዳሽን ቢራ ፋብሪካን ለአንድ የውጭ ኩባንያ በ90 ሚሊዮን ዶላር ከእውቅና ውጭ የተሸጠ ሰለመሆኑና ማስረጃውንም ማግኘት ያልተቻለ በመሆኑ የተሟላ ክስ ለመመስረትና ማስረጃ ለመሰብሰብ የጊዜ ቀጠሮ ጠይቋል።

የክስ ጉዳያችን አዲስ አበባ ሊታይና ልንዳኝ ይገባል ያሉትንም ወንጀሉ ተፈፅሟል ተብሎ የሚጠረጠረውና ሃብቱ የሚገኘው በክልሉ በመሆኑ የክርክር ጉዳዩ በዚሁ እንዲታይ ለችሎቱ አቅርቧል።

የግራ ቀኙን ክርክር ያዳመጠው ችሎቱ ተከሳሾች በቤተሰቦቻቸው እንዲጎበኙና እንደማንኛውም ዜጋ ህገ-መንግስታዊ መብታቸው ተከብሮ ችሎቱን እንዲከታተሉ ፈቅዷል።

ተከሳሾቹ የፍርድ ሂደታቸውን በዚሁ እንዲከታተሉ፣ ለደህንነታቸው ጥብቅ ጥበቃ እንዲደረግና ከዛሬ ጀምሮ ወደ ማረሚያ ቤት እንዲሄዱም አዟል።

አቃቢ ህግ ያቀረበውን ቀሪ መረጃ የማጠናቀሪያ የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄን ያዳመጠው ፍርድ ቤቱ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ በመስጠት ለየካቲት 1/2011 ዓ.ም. እንዲቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም