'ለሥራ የተሰጠንን ህንፃ ያለማስጠንቀቂያ እንድንለቅ ተደርገናል' ሲሉ በጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ የተሰማሩ ገለፁ

73

አዲስ አበባ  ጥር 16/2011 በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ለሥራ የተሰጠንን ባለአራት ወለል ህንፃ ያለምንም ማስጠንቀቂያና ተለዋጭ ቦታ እንድንለቅ ተደርገናል ሲሉ በጥቃቅንና አነስተኛ የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ማህበራት ገለፁ።

በጠቅላላው 92 የሚሆኑት ማህበራቱ በ2009 እና 2010 ዓ.ም ከክፍለ ከተማው ጥቃቅንንና አነስተኛ ቢሮ ጋር ተዋውለው የመስሪያ ቦታው እንደተሰጣቸው ይናገራሉ።

ሆኖም በአካባቢው ውሃና መብራትን የመሰሉ መሰረተ ልማቶች በጊዜው ባለመሟላታቸው ወደስራ ሳይገቡ ሁለት ዓመት ማሳለፋቸውን የሚናገሩት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፤ ካለፈው መስከረም 2011 ዓም ጀምሮ ግን የተወሰኑት ሥራ መጀመራቸውን ለኢዜአ ገልፀዋል።

በዚህ ወቅት ግን ከዚህ በፊት ከክፍለ ከተማው ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ ጋር የተደረገው ውል ፈርሶ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፕሬሽን ጋር በድጋሚ እንዲዋዋሉ መደረጉንም አንሰተዋል።

የተወሰኑት ሥራ ጀምረዋል፤ አንዳንዶቹ ደግም ዝግጅታቸውን ጨርሰው ስራ ለመጀመር ዝግጁ በሆኑበት ወቅት ነው የተሰጣቸው ህንጻው የታሸገው ሲሉ ነው የማህበራቱ አባላት የተናገሩት። 

በአሁኑ ወቅት የማምረቻና መሸጫ ህንጻው በአካባቢው ለሚገኘውና የመማሪያ ክፍሎች እጥረት ገጥሞታል ለተባለው 'የጋራ ጉሪ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት' በጊዜያዊነት ተሰጥቷል። 

በባህል አልባሳት ሽያጭ የተሰማሩት ወይዘሮ ባንቺ አለም ውቤ እና ወይዘሮ በላይነሽ መላኩ ቦታውለሽያጭ አመቺ ባለመሆኑ ሽያጭ የሚያከናውኑት በተለያዩ አካባቢዎች በሚዘጋጁ የንግድ  ባዛሮች እና በየቦታው እያዞሩ መሆኑን ገልፀዋል።

ህንፃው የታሸገውም እነርሱ በሌሉበት ንብረታቸውን ሳያወጡና ምትክ ቦታ ሳይሰጣቸው መሆኑንም ይናገራሉ።

የንግድ ፍቃድ ለማውጣትና ወደስራ ለመግባት ብዙ ውጣ ውረድ አልፈው ስራ ሊጀምሩ ሲል የመስራያ ቦታውን መነጠቃቸውን የገለጹት ደግሞ ሌላዋ ቅሬታ አቅራቢ ወይዘሮ አበባ ደምሴ ናቸው።

በህንጻ መሳሪያ ሽያጭ የተሰማራው ወጣት አሊ አበበና  በካፌና ሬስቶራንት ስራ የተሰማራው ወጣት ፍቃዱ ከበደ የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፕሬሽን ባለፈው መስከረም ወር ላይ ማህበራቱን ሰብስቦ አብሮ ለመስራት የ3ዓመት ውል መደረጉን  ያነሳሉ። 

ኮርፕሬሽኑ በማህበራቱ በኩል ስምምነቱ የሚያፈርስ ችግር ከተፈጠረ በቅድሚያ ሊያሳውቀንና መፍትሄም ሊሰጠን ይገባ ነበር ሲሉም ተናግረዋል።

ማህበራቱ የቦሌ ክፍለ ከተማ ጥቃቅንና አነስተኛ ቢሮ መፍትሄ እንዲሰጣቸው በተደጋጋሚ ቢጠይቁም መፍትሄ እንዳላገኙም ተናግረዋል።

በተሰማሩበት ስራ ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን የሚያስተዳድሩ መሆኑን ገልጸው ፈጣን ምላሽ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል።

ህንጻውን በጊዜያዊነት የተረከበው የጋራ ጉሪ የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር አቶ ከድር ጃርሶ በበኩላቸው በመማሪያ ክፍሎች እጥረት ችግር ሳቢያ ተማሪዎችን በሶስት ፈረቃ ለማስተማር መቸገራቸውን አንስተዋል።

በአካባቢው የሚገኝና አገልግሎት የማይሰጥ ህንጻ መኖሩን ከማህበረሰቡ ጥቆማ እንደደረሳቸውና ህንፃው ይሰጣቸው ዘንድም ለአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ  ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት ህንጻውን በጊዜያዊነት መረከባቸውን ነው የተናገሩት።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የአነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንደስትሪ ክላስተር ልማት ኮርፕሬሽን ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ሀሺቅ በድሩ በስልክ ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በሰጡት ቃል በህንጻው የመስሪያ ቦታዎች ላይ በተደጋጋሚ ባደረጉት ምልከታ አብዛኛው ማህበራት ወደ ስራ አለመግባታቸውን ይናገራሉ።

ከማህበራቱ ጋር በተደረገው ስምምነት መሰረት ማህበራት ወደስራ ካልገቡ ውል ማቋረጥ የሚቻል በመሆኑ ውላቸው እንዲቋረጥ ተደርጓል ብለዋል።

ሆኖም እርምጃው ከተወሰደ በኋላ ማህበራቱ ወደ ስራ ለመግባት ያጋጠማቸውን ችግሮች በመገንዘብ በየካ አያት ሳይት ላይ ምትክ ቦታ እንዲሰጣቸው ተወስኗል ነው ያሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም