በኦሮሚያ የጤና አገልግሎትን ተደራሽነትን ለማረጋገጥ የዘርፉ ቦርድ አባላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ

88

አዳማ ጥር 16/2011 በኦሮሚያ ክልል የጤና አገልግሎቱን ፍትሃዊነት፣ጥራትና ተደራሽነት  ለማረጋገጥ የዘርፉ  የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ተጠየቀ፡፡

በክልሉ በየደረጃው ለሚገኙ ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የሥራ አመራር ቦርድ አባላት የተዘጋጀ የግምገማ መድረክ ዛሬ በአዳማ ከተማ ተጀምሯል።

በዚህ ወቅት የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ደረጀ ዱጉማ እንዳሉት  የጤና አገልግሎት ፍትሃዊነትና ጥራት እንዲረጋገጥ ለማስቻል ለስራ አመራር ቦርድ አባላት ከፍተኛ ኃላፊነት ተሰጥቷል።

ሆኖም  በቁርጠኝነት ማነስና በአመራሮች መቀያየር ምክንያት የቦርድ አባላቱ የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነትና ተግባር በአግባቡ እየተወጡ እንዳልሆነ ገልጸዋል።

በክልሉ የጤና አገልግሎቱን ፍትሃዊነት፣ጥራትና ተደራሽነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሆስፒታሎችና የጤና ጣቢያዎች የሥራ አመራር ቦርድ አባላት ተሳትፏቸውን እንዲያጠናክሩ ጠይቀዋል።

በተለይ በክልሉ እናቶች ቤት ከመውለድና ከጽዳት ጉድለት  ነፃ ከማድረግ ፣ በጤና ኢንሹራንስ አተገባበር እንዲሁም በጤና ተቋማት እየተካሄደ ባለው ሪፎርም አኳያ የቦርድ አመራሮች እያበረከቱ ያለውን ድጋፍና ክትትል ለመገምገም መድረኩ መዘጋጀቱን ጠቁመዋል።

በትምህርት ቤቶች ኤች አይቪን መከላከሉ ስራ አመራሩ አጀንዳ አድርጎ በመንቀሳቀስ ረገድ፣በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብሩ የታየውን መቀዛቀዝ ማስተካካል በሚቻልበት ጉዳይ ላይ በመምከርና ሂስና ግለ ሂስ በማካሄድ የቀጣይ አቅጣጫ እንደሚቀመጥ ይጠበቃል።

የክልሉ ጤና ጥበቃ ቢሮ ምክትል ኃላፊ  ዶክተር አብዱቃድር ገልገሎ በበኩላቸው በክልሉ ጤናማና ምርታማ የሆነ ማህበረሰብ ለማፍራት ብቃትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በ79 ሆስፒታሎች የሪፎርም ስራ መጀመሩን ገልጸዋል፡፡

ሪፎርሙን በመተግበር ደረጃውን የጠበቀ የህክምና አገልግሎት በመስጠት በኩል ኦለንጪቲ፣ኩዩ፣ ሸናን ጊቤ፣ ቢሾፍቱ፣ነጆ፣ጉደርና ቢሲዱም ሆስፒታሎች በተሻለ ደረጃ እንደሚገኙ አመልክተዋል።

ወደ ኋላ ከቀሩት ሆስፒታሎች ውስጥ  ጭሮ፣ሞጆ፣ገለምሶ፣ሞያሌ፣ዳሪሙ፣ቀርጫ፣አዶላና መልካ ሶዶ ሆስፒታሎች ይገኙበታል። 

በክልሉ ጤናማና ምርታማ የሆነ ማህበረሰብ ለማፍራት ብቃትና ጥራት ያለው የጤና አገልግሎት ለህብረተሰቡ ለማዳረስ በሆስፒታሎች የተጀመረው የሪፎርም ስራ  ተጠናክሮ መቀጠል አለበት።

ከመድረኩ ተሳታፊዎች መካከል የኦለንጪቲ ሆስፒታል ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው ታምራት በሰጡት አስተያየት ሆስፒታሉ የተሻለ ደረጃ ላይ እንዲደርስ ቦርዱ እቅድ በማውጣት የቅርብ ድጋፍና ክትትል ማድረጉን ገልጸዋል።

በሆስፒታሉ የተገኘውን ልምድና ተሞክሮ በምስራቅ ሸዋ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ለማስፋፋት ቦርዱ ትስስርና ተሳትፎውን በማጎልበት የተቋማቱ የጤና አገልግሎት ጥራት እንዲሻሻል በቅርበት እየሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

ለሁለት ቀናት በተዘጋጀው የግምገማው መድረክ  ከክልሉ ሁሉም ዞኖችና 19 የከተማ አስተዳደሮች  የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም