በኢሉአባቦር ዞን ከ4 ነጥብ 4 ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል

1089

መቱ ጥር 16/2011 በኢሉ አባቦር ዞን  በግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ ያለው ምርት መገኘቱን የዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት አስታወቀ፡፡

በዞኑ እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ጽህፈት ቤት የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ብርሃኑ ኢረና ለኢዜአ እንደገለጹት በዞኑ 13 ወረዳዎች በ135 ሺህ 500 ሄክታር መሬት ላይ ከለማው ሰብል አራት ነጥብ አራት ሚሊዮን ኩንታል ምርት ተሰብስቧል፡፡

በወቅቱ  የተገኘው ምርት መጠን ከቀዳሚው ዓመት የምርት ወቅት ጋር ሲነፃፀር  በግማሽ ሚሊዮን ኩንታል ብልጫ አለው፡፡

በሰብል የነበረው የምርታማነት መጠንም በሄክታር ከ30 ኩንታል ወደ 33 ኩንታል ማደጉን ነው የተናገሩት፡፡

ለምርታማነት ማደጉ የአርሶ አደሩ የግብአት ፣ምርጥ ዘርና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ፍላጎትና ባህል እያደገ መምጣት በዋናነት እንደሚጠቀስ ተናግረዋል፡፡

በምርት ወቅቱ ከለማው መሬት 25 ሺህ ሄክታር ምርጥ ዘር፣ግብአትና የመስመር ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተሟላ ፓኬጅ የለማ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በወቅቱ በተሟላ ፓኬጅ የለማው መሬት መጠንም ካለፈው ምርት ወቅት ጋር ሲነጻጸር ከ5ሺህ ሄክታር በላይ ብልጫ እንዳለው ተናግረዋል፡፡

በሁሩሙ ወረዳ ቶማ ዮቢ ቀበሌ አርሶአደር ወይዘሮ ብርሃኔ ፍሪሳ በሰጡት አስተያየት በአንድ ሄክታር  መሬት በቆሎ፣ጤፍና የተለያዩ ቋሚ ሰብሎችን አልምተዋል፡፡

”ካለማሁት መሬት ግማሽ ያህሉን ምርጥ ዘር ፣ማዳበርያና የመስመር ቴክኖሎጂ በመጠቀም በተሟላ ፓኬጅ ነው ያለማሁት” ያሉት አርሶ አደሯ ይህም የተሻለ ምርት እንዳስገኘላቸው ተናግረዋል፡፡

በልማቱም 20 ኩንታል ምርት መሰብሰባቸውንና ባለፈው ዓመት ካገኙት ከእጥፍ በላይ ብልጫ እንዳለው ነው የገለጹት፡፡

በመቱ ወረዳ ቡሩሳ ቀበሌ አርሶአደር አለማየሁ ፈይሳ በበኩላቸው ከአንድ ሄክታር ተኩል በላይ መሬት ላይ በቆሎ፣ማሽላ፣አደንጓሬ፣ጤፍና የአተር ሰብሎች አልምተዋል፡፡

በምርት ዘመኑ የሰበሰቡት ምርት መጠን ካለፈው ዓመት በእጥፍ ብልጫ እንዳለው  ተናግረዋል፡፡

በኢሉአባቦር ዞን ከ150ሺ በላይ አርሶአደሮችን በማሳተፍ በወቅቱ የለሙት በአብዛኛው የበቆሎ፣ማሽላ፣ገብስ፣አተር፣ባቄላ፣ አደንጓሬ፣ሩዝ  የመሳሰሉ የአገዳ ብዕርና የቅባት ሰብሎች ናቸው፡፡