የጠረፍ ንግድ ስርዓቱን ማሻሻል የሚያስችል ሰነድ እየተዘጋጀ ነው – የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር

1153

አዲስ አበባ   ጥር 16/2011 ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጠረፍ ንግድ ስርዓቱን ማሻሻል የሚያስችል ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ገለጸ።

ሚኒስቴሩ በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት የኮንትሮባንድ ንግድ እንዲስፋፋና ምርቶች በድንበር በኩል በህገ-ወጥ መንገድ እንዲወጡ እድል ፈጥሯል ብሏል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በዛሬ መደበኛ ስብሰባው የመስሪያ ቤቱን የ2011 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ገምግሟል።

ሚኒስትሯ ወይዘሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሄር ባለፉት ጊዜያት በአገሪቱ ተከስቶ የነበረው አለመረጋጋት የወጪ ንግድ ገቢ እንዲቀንስ ማድረጉን ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

በምክንያትነት ያቀረቡት ደግሞ የነበረው ያለመረጋጋት ሁኔታ ምርቶች በሚፈለገው መጠን እንዳይንሸራሸሩና ወደ ውጭ አገራት እንዳይንቀሳቀሱ ማድረጉን ነው።

የአገሪቱ የሎጂስቲክስ ስርዓት ውድ መሆንና ተወዳዳሪ የገበያ ስርዓት አለመኖርም ለወጪ ንግዱ ገቢ መቀነስ ምክንያቶች መሆናቸውን ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ ስድስት ወራት ከወጪ ንግድ 1 ነጥብ 96 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ታቅዶ ማሳካት የተቻለው 1 ነጥብ 21 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነም ነው የገለጹት።

ይህ አፈጻጸም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጊዜ ከተገኘው 1 ነጥብ 35 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ጋር ሲነጻጸር የ10 በመቶ ቅናሽ አሳይቷል። 

መስሪያ ቤታቸው በቀጣይ አገሪቱ ከዘርፉ ማግኘት የሚገባትን ጥቅም እንድታገኝ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ተቀናጅቶ ችግሩን ለማስወገድ እንደሚሰራ ለምክር ቤቱ ገልጸዋል።

ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን ሕገ-ወጥ የንግድ እንቅስቃሴዎችን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የጠረፍ ንግድ ስርዓቱን ማሻሻል የሚያስችል ሰነድ እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቁመዋል።

የምክር ቤቱ የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ጌታቸው መለሰ የአገር በቀል ምርቶችን ከማምረት አቅምና ጥራትን ከማሳደግ ባሻገር ቀልጣፋና የላቀ ገበያን የማስፋት ክፍተት መኖሩን ተናግረዋል።

ለአገር ውስጥ ምርቶች አስተማማኝና የተሻሉ የገበያ መዳረሻዎችን የሚፈጥሩና ኢንቨስትመንትን የሚያስፋፉ ተግባራትን ማጠናከር እንደሚያስፈልግ በመጠቆም።

አገሪቱን ከአካባቢያዊ ውህደት ተጠቃሚ ለማድረግና ለላኪዎች የገበያ ትስስር በመፍጠር ረገድ የተጠናከረ ስራ እንደሚጠበቅም አክለዋል።

ሚኒስቴሩ የገበያ መዳረሻዎችን በማስፋት የወጪ ንግዱን ማሳደግ ላይ ትኩረት እንዲያደርግም ቋሚ ኮሚቴው አሳስቧል።