ዲፕሎማቶች በባህላቸው የሚኮሩና የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ መሆን አለባቸው - የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

127

አዲስ አበባ ጥር 16/2011 ዲፕሎማቶች በባህልና ታሪካቸው የሚኮሩና በሄዱበት የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁ እንዲሆኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አሳሰበ።

በሚኒስቴሩ የውጭ ግንኙነት አገልግሎት ማሰልጠኛ ኢንስቲትዩትና የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት በመተባበር የወጣት ሰልጣኝ ዲፕሎማቶች ስልጠና እየሰጡ ነው።

ከኢትዮጵያ ህዝብ 70 በመቶ ያህሉ ከ30 ዓመት በታች የዕድሜ ክልል ውስጥ እንደሚገኙ ጥናቶች ያሳያሉ።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ ብርቱካን አያኖ እንዳሉት፤ በተለያዩ አገራት ኢትዮጵያ የምትልካቸው ወጣት ዲፕሎማቶች የአገራቸውን ባህልና እሴት ጠብቀው ለዓለም የሚያንጸባርቁ መሆን አለባቸው።

ኢትዮጵያ የምታሰማራቸው ወጣት ዲፕሎማቶች የአገራቸውን ባህልና፣ ወግ፣ እሴትና ትውፊት በመግለጽ የታላቅ አገር ዜጋ መሆናቸውን ማሳየት ይኖርባቸዋል ነው ያሉት።

ወጣቶች የኢትዮጵያን መፃኢ ዕድል የሚወስኑ መሆናቸውን በመገንዘብ በሥነ-ምግባር የታነጹ፣ በዕውቀት የበለጸጉ፣ በአገራቸው የሚኮሩ እንዲሆኑም አሳስበዋል።

"ኢትዮጵያ ከሌላው ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት ማሳመርም ሆነ ማበላሸት በወጣት ዲፕሎማቶች ላይ የወደቀ ነው" ያሉት ሚኒስትር ዴኤታዋ ዲፕሎማቶቹ አገራዊ ኃላፊነታቸውን በብቃት እንዲወጡ አሳስበዋል።

የሚኒስቴሩ የሴቶች ህፃናትና ወጣቶች ጽህፈት ቤት ዳይሬክተር ጀነራል ወይዘሮ አልማዝ ገበያው ወጣቶች በሥነ-ምግባር፣ በእውቀትና በክህሎት እንዲዳብሩ በቅድሚያ ከአደንዛዥ ዕጾችና ደባል ሱሶች መራቅ አለባቸው ብለዋል።

ኢትዮጵያን ወክለው በሚሄዱባቸው አገሮችም አገር ወዳድ፣ ብሔራዊ ጥቅምን የሚያስከብሩና ኃላፊነት የሚሰማቸው መሆን አለባቸው ብለዋል።

ይህን መሰሉ ስልጠና ሲሰጥ የአሁኑ ለአራተኛ ጊዜ ሲሆን ከ220 በላይ ወጣት ሰልጣኝ ዲፕሎማቶች በተለያዩ ጉዳዮች ላይ የአንድ ዓመት ስልጠና ተከታትለዋል።

ስልጠናው የሚሰጠው የወጣቶችን የዲፕሎማሲ ክህሎት ለማዳበር በፐብሊክ፣ በኢኮኖሚያዊና በፖለቲካ ዲፕሎማሲ ዘርፍ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም