የለውጡን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም ልማትን እንደሚደግፉ በውጪ የሚኖሩ የዳባት ተወላጆች ተናገሩ

336

ጎንደር ጥር 15/2011 ሀገራዊ ለውጡ የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በትውልድ አካባቢያቸው የተጀመሩ የልማት ስራዎችን እንደሚደግፉ በውጪ የሚኖሩ በሰሜን ጎንደር ዞን የዳባት ከተማ ተወላጆች ተናገሩ፡፡

ተወላጆቹ በዳባት ከተማ ጧሪና ደጋፊ ያጡ አረጋውያንና ህጻናትን ለመደገፍ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ትናንት በጎንደር ከተማ በተዘጋጀው መርሃ ግብር ላይ ተሳትፈዋል፡፡

ከተሳታፊዎቹ መካከል በአሜሪካ የሚኖሩት አቶ ተስፋሁን አረጋዊ እንደተናገሩት በውጪ የሚኖሩ የከተማውን ተወላጆች በማስተባበር በ650ሺህ ብር ወጪ አንድ ቤተ መጻህፍት ተገንብቷል፡፡

ቤተ-መጻህፍቱን ስራ ለማስጀመር እንዲቻልም በግላቸው 80 ወንበርና 10 ጠረጴዛ አሰርተው ለማሰረከብ ቃል ገብተዋል፡፡

ሌላው በውጪ  የሚኖሩት ወይዘሮ ፍሬህይወት ደርሶ የተባሉ የከተማው ተወላጅ በበኩላቸው በከተማው ለተቋቋመው የህጻናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር የገንዘብ ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸውን አስታውሰዋል፡፡

በማህበሩ የተሰባሰቡ አረጋውያንና ህጻናት ከተረጂነት  ተላቀው የራሳቸውን ገቢ ፈጥረው ኑሮአቸውን መምራት እንዲችሉም ማህበሩ ለሚያደርገው የመልሶ መቋቋም ስራ ድጋፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል፡፡

በቅርቡ በአዲስ አበባ ያቋቋሙትን የጡት ካንሰር የህክምና ማዕከል በጎንደር በመክፈት ለበሽታው ተጋላጭ ሴቶች ነጻ የህክምና ድጋፍ ለመስጠት መዘጋጀታቸውንም አመልክተዋል፡፡

“ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ዲያስፖራው ሀገራዊ ተሳትፎውን በማጠናከር እውቀቱንና ገንዘቡን አቀናጅቶ ሀገሩንና አካባቢውን ለመደገፍ ተዘጋጅቷል ” ያሉት ደግሞ አቶ እባቡ በላይ የተባሉ በአሜሪካ የሚኖሩ የከተማው ተወላጅ ናቸው፡፡

“ትውልድ ተምሮ በእውቀት ካልታነጸ እድገትና ልማት ፈጽሞ አይታሰብም “ያሉት አቶ እባቡ እሳቸውን ጨምሮ ሌሎችም  ዲያስፖራዎች ለአካባቢያቸው  ልማት ትኩረት በመስጠት ለመደገፍ ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በሀገሪቱ የተፈጠረውን ምቹ ሁኔታ በመጠቀም በትውልድ አካባቢያቸው የተጀመሩ የልማት ስራዎች መደገፋቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተወላጆቹ በሰጡት አስተያየት ገልጸዋል፡፡

የዳባት ህጻናትና አረጋውያን መርጃ ማህበር አስተባባሪ አቶ ሙሉቀን ሲሳይ በበኩላቸው በውጪ የሚኖሩ የከተማው ተወላጆች ማህበሩ ለሚረዳቸው 55 ህጻናትና አረጋውያን ከግማሽ ሚሊዮን ብር በላይ ድጋፍ ማድረጋቸውን አስታውቀዋል፡፡

በተጨማሪም ለ228 ችግረኛ ተማሪዎች ለእያንዳንዳቸው የትምህርት ቤት የደንብ ልብስና የትምህርት ቁሳቁስ ገዝተው በመስጠት ዲያስፖራው እገዛ እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

“ዲያስፖራዎች ለአካባቢያቸው ልማት የሚያደርጉት ድጋፍ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ጽህፈት ቤቱ ከጎናቸው ይቆማል” ያሉት ደግሞ የሰሜን ጎንደር ዞን የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ /አዴፓ/ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ጌታሁን ናቸው፡፡

ዲያስፖራዎች በዞኑ አዋጭ በሆኑ የኢንቨስትመንት መስኮች ተሰማርተው እራሳቸውንና አካባቢያቸውን ተጠቃሚ እንዲያደርጉም የዞኑ መስተዳድር ማናቸውንም ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በመርሃግብሩ ላይ በሀገር ውስጥና በውጪ የሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆች ፣ባለሀብቶች፣ ወጣቶችና ሴቶች እንዲሁም የከተማውና የዞኑ አመራሮች ተሳታፊ ሆነዋል፡፡