የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ለአካባቢው ሰላም መሰረት መሆኑን የኩዌት አሚር ገለፁ

70

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 የኢትዮጵያና የኤርትራ የሰላም ስምምነት ለአካባቢው ሰላም መሰረት መሆኑን የኩዌቱ አሚር ሼክ ሳባህ አል-አህመድ አል ጃቢር አል ሳባህ ገለጹ።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ያደረጉት የሰላም ስምምነት ከሁለቱ አገራት ጥቅም በተጨማሪ ለአካባቢው ሰላም መስፈን መሰረት መሆኑን የገለጹት አሚሩ፤ የኢትዮ-ኩዌት ግንኙነት በጠንካራ መሰረት ላይ እንደሚገኝም አስታውቀዋል።

የኩዌቱ አሚር ይህን የገለጹት በኩዌት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሆነው የተሾሙት ክቡር አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ የሹመት ደብዳቤያቸውን ትናንት ለአሚሩ ባቀረቡበት ወቅት እንደሆነ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።

አምባሳደር አብዱልፈታህ አብዱላሂ አገራችን እያካሄደች ስላለው ለውጥ ለአሚሩ ገለጻ አድርገዋል።

የኩዌቱ አሚር በበኩላቸው በሁለቱ አገራት መካካል ያለው ጠንካራ ወዳጅነት መጠናከሩን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ በአፍሪካ ቀንድ ሰላም እንዲሰፍን የምታደርገውን ጥረት እንዲሁም ከኤርትራ ጋር የነበራትን አለመግባባት በሰላም ለመፍታት ከኤርትራ ጋር ያደረገችውን ስምምነት አድንቀዋል።

የኢትዮ-ኤርትራ ስምምነቱ ለአካባቢው ሰላም መሰረት ነውም ብለዋል።

ኢትዮጵያና ኩዌት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት የጀመሩት እ.ኤ.አ በ1967 ሲሆን፤ በየአገራቱ ኤምባሲዎቻቸውን የከፈቱት ግን እ.ኤ.አ በ1997 እንደሆነ ከቃል አቀባይ ጽህፈት ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም