በክልሎች ሐኪሞችን ተቀብሎ መመደብ አለመቻል ፈተና ሆኗል - የጤና ሚኒስቴር

56

አዲስ አበባ ጥር 15/2011 ክልሎች የሚላኩላቸውን ሐኪሞች ተቀብለው መመደብ አለመቻል ትልቅ ፈተና መጋረጡን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

ሚኒስቴሩ የ2011 በጀት ዓመት የስድስት ወራት አፈጻጸሙን ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አቅርቧል።

ሚኒስትሩ ዶክተር አሚር አማን እንደተናገሩት በአሁኑ ወቅት ክልሎች በበጀት እጥረትና ሌሎች ምክንያቶች ሐኪሞችን መቀበል እያቆሙ ነው።

ለሚኒስቴሩ ቀጥታ ተጠሪ የሆኑት የፌዴራል ሆስፒታሎች አራት ብቻ በመሆናቸው ሐኪሞችን የመመደብ አቅሙ አነስተኛ እንደሆነም አስታውቀዋል።

እንደ ዶክተር አሚር ገለጻ የዓለም ጤና ድርጅት በጣም ድሃ በሚባሉ አገራት ለአንድ ሺህ ሰዎች በአማካይ 4 አዋላጅ ነርሶች፣ ነርሶችና ሐኪሞች ምጥጥን ሊኖር እንደሚገባ ያስቀምጣል።

በአሁኑ ወቅት በኢትዮጵያ የጤና መኮንኖች፣ ነርሶች፣ የአዋላጅ ነርሶችና ሐኪሞች ቁጥር ለአንድ ሺህ ሰዎች ሲካፈል ምጥጥኑ 0 ነጥብ 9 መሆኑን አስረድተዋል።

ዝቅተኛውን የዓለም የጤና ድርጅት መስፈርት ለማሟላት ምጥጥኑን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ በሚያስፈልግበት ነባራዊ ሁኔታ ክልሎች ሐኪሞችን መቀበል ማቆማቸው አሳሳቢ መሆኑን ነው ያመለከቱት።

በክልሎች ሐኪሞችን መቀበል አለመቻል የሐኪሞች ስልጠና ቁጥር እንዲቀነስ ከተደረገ ደግሞ በቀጣዮቹ ዓመታት እጥረት ሊያጋጥም እንደሚችልም ስጋታቸውን ገልጸዋል።

ሚኒስቴሩ ሐኪሞች በጤና ጣቢያዎች እንዲመደቡ በማድረግ፣ በጤና ኤክስቴንሽን መርሃ ግብር በማካተትና ከክልሎች ጋር በቅርበት በመስራት ችግሩን ለመፍታት እየሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

ክልሎች ለጤናው ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥተው የበጀት እጥረት ችግሩ እንዲፈታም የምክር ቤቱንና የባለድርሻ አካላትን እገዛ ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም